Saturday, September 21, 2024
spot_img

የኢትዮጵያን የውጭ የዕዳ ጫና ለማቅለል የተቋቋመው የአበዳሪዎች ኮሚቴ የመጀመርያ ስብሰባ ተካሄደ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ መስከረም 19፣ 2014 ― የኢትዮጵያ መንግሥት የገጠመውን ከፍተኛ የውጭ ብድር የዕዳ ጫና ለማቃለል በጠየቀው መሠረት የተቋቋመው ዓለም አቀፍ የአበዳሪዎች ኮሚቴ የመጀመርያ ውይይቱን አካሄዷል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ያቀረበውን የውጭ ዕዳ ጫና ማቅለያ ጥያቄ ለመገምገም የተቋቋመው የአበዳሪዎች ኮሚቴ የመጀመርያ ስብሰባውን መስከረም 18፣ 2014 በበይነ መረብ አማካይነት ማድረጉን ፓሪስ ክለብ በመባል የሚታወቀው የአበዳሪ አገሮች ቡድን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

በዚህ ውይይት ላይም የገንዘብ ሚኒስትር የሆኑት አቶ አሕመድ ሺዴ የኢትዮጵያን የዕዳ ጫና ማቅለያ ጥያቄ እንዳቀረቡና ማብራሪያ እንደሰጡ አስታውቋል፡፡

በሰኔ ወር 2013 መጨረሻ ላይ 29.5 ቢሊዮን ዶላር የደረሰው የኢትዮጵያ አጠቃላይ የውጭ ዕዳ መጠን፣ አገሪቱ ተጨማሪ ብድር የማግኘት ፍላጎቷን መገደቡ የሚታወቅ ሲሆን፣ ይህ የብድር ጫና የመክፈያ ጊዜ ማራዘሚያና የዕዳ መክፈያ የእፎይታ ጊዜ አማራጮች ለማቅለል፣ ከተቻለም የዕዳ ስረዛን በማስፈቀድ የብድር ጫናው እንዲቀልለት፣ የቡድን 20 አገሮች በፈቀዱት የዕዳ ማቅለያ ሥርዓት አማካይነት የኢትዮጵያ መንግሥት ጥያቄ አቅርቧል መባሉንም የሪፖርተር ጋዜጣ ዘገባ አመልክቷል።

ይህን የዕዳ ጥያቄ ማቅለያ ለመገምገም 12 አገሮችን በአባልነት የያዘ የአበዳሪዎች ኮሚቴ መስከረም 6፣ 2014 በይፋ የተቋቋመ ሲሆን፣ ኮሚቴውንም ለኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ብድር የሰጡት ቻይናና ፈረንሳይ በሊቀመንበርነት እንደሚመሩት ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ከውጭ አበዳሪዎቹ የዕዳ ጫና ማቅለያ በሆኑት አማራጮች የዕዳ መክፈያ ጊዜ ማራዘሚያ የዕዳ መክፈያ እፎይታ ጊዜ፣ እንዲሁም ለተጨማሪ የውጭ ብድር ከእነዚህ አገሮች ዋስትና ካልተሰጠው ተጨማሪ የውጭ ብድር የማግኘት ዕድሉ የተዘጋ መሆኑን ባለሞያዎች ይገልጻሉ፡፡

የኢትዮጵያ አበዳሪ አገሮች ባቋቋሙት የአበዳሪዎች ኮሚቴ አማካይነት የዕዳ ማቅለያ እንደሚገኝ በማመንም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍ ብድር እንዲመቻችለት መጠየቁ ታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ ላለባት የብድር ጫና ማቅለያ እንደምታገኝ ታሳቢ በማድረግ አይኤምኤፍ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ለማበደር ተስማምቶ የነበረ ቢሆንም፣ የማበደሪያ ጊዜ ገደቡ በዚህ ወር ማብቂያ እንደሚጠናቀቅ ታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ በዚህ ዕድል መጠቀሚያ ጊዜው እየተጠናቀቀ ባለበት በዚህ ወር የኢትዮጵያን የዕዳ ጫና ለማቅለል የአበዳሪዎች ኮሚቴ መቋቋሙ የፈነጠቀውን ተስፋ በመጠቀም፣ አዲስ ብድር እንዲምቻችለት የኢትዮጵያ መንግሥት ለአይኤምኤፍ ጥያቄ ማቅረቡን፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ከሳምንት በፊት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ ካለባት አጠቃላይ የውጭ ብድር ውስጥ ከ14 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚሆነው ከቻይና መንግሥት የተገኘ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img