አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ መስከረም 19፣ 2014 ― የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ እርዳታ ጫኝ መኪኖች ወደ ትግራይ አንዲንቀሳቀሱ ጠይቀዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የአስቸኳይ ጊዜ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትስ በትግራይ ረሃብ ጉዳት እያስከተለ ነው ብለው እንደሚያስቡም ለሬውተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል። ኃላፊው ይፋዊ ባልሆነ የሰብዓዊ እርዳታ እቀባ ስር በምትገኘው ትግራይ መድረስ ከሚኖርበት የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት 10 በመቶ ብቻ ለተረጂዎች መድረሱንም ለዜና ወኪሉ ገልጸዋል።
ማርቲን ግሪፊትስ ጨምረውም ጥያቄያቸው እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች እንዲንቀሳቀሱ መፍቀድ መሆኑን በትላንትናው እለት ተናግረዋል። “ይህ ሰው ሰራሽ ነው፤ በመንግሥት እርምጃ ሊሻሻል ይችላል” ሲሉ የተመድ የሰብዓዊ እርዳታ ኃላፊው ገልጸዋል።
ከ10 ወራት በፊት በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል ግጭት ከተከሰተ በኋላ በሺዎች የሚቀጠሩ በግጭቱ ስለመሞታቸው፤ እንዲሁም በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች አስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው በተደጋጋሚ ሲዘገብ ቆይቷል።
“ረሃብ በሚመስል ሁኔታ ውስጥ 400 ሺህ ሰዎች ይገኛሉ ብለን ተንብየን ነበር፤ ግምታችን የነበረው እርዳታ የማይደርሳቸው ከሆነ ለረሃብ ይጋለጣሉ የሚል ነው” በማለት ግሪፊትስ የመንግሥታቱ ድርጅት ሰኔ ወር ላይ የነበረውን ትንበያ አስታውሰዋል።
ግሪፊትስ በትግራይ የነዳጅ፣ የጥሬ ገንዝብ፣ የተሸከርካሪዎች እጥረት እና ይፋዊ ያልሆነ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እቀባ መኖሩን በማስታወስ “ይህን የመሰለ ነገር (ረሃብ) ተከስቷል ብዬ መገመት አለብኝ” ተናግረዋል።
መንግሥት በበኩሉ የሰብዓዊ እርዳታ እንዳይቀርብ ምንም አይነት እቀባዎችን አለመድረጉን ሲያሳውቅ ቆይቷል። ይልቁንም የእርዳታ ቁሳቁሶች ወደ ክልሉ በፍጥነት እንዲገቡ ለማቀላጠፍ ሰባት የነበሩትን የፍተሻ ጣቢያዎች ወደ ሁለት እንዲቀነሱ ማድረጉን መንግሥት አስታውቆ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት የእርዳታ ቁሳቁሶችን ጭነው ወደ ትግራይ ክልል ተጉዘው ከክልሉ ሳይወጡ የሚቀሩት ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎቹ በክልሉ ውስጥ ለምን አገልግሎት እየዋሉ እንደሆነ ግልጽ ባለመሆኑ ጥርጣሬን ፈጥሮብኛል ሲል ነበር።