አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ መስከረም 19፣ 2014 ―
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ (ባልደራስ) በእስር ላይ የሚገኙት አመራር አባሉ አቶ ሥንታየሁ ቸኮል ሕመም እንዳጋጠማቸው በመጥቀስ ሕክምና የማግኘት መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ለኢሰመኮ በጻፈው ደብዳቤ ጠይቋል።
የኩላሊት ህመም እንደገጠማቸው የተገለጸው አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ የተሻለ ህክምና አግኝተው ማግኘት እንዲችሉ ማረሚያ ቤቱን ደጋግመው ቢጠይቁም ጥያቄቸው ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱን ፓርቲው አሳውቋል።
በዚሁ የተነሳ በኩላሊት ህመም ምክንያት ሌት ተቀን እየተሰቃዩ ቆሞ እንኳን ቤተሰባቸውን ማነጋገር እያቃታቸው ስለመሆኑም ባልደራስ በደብዳቤው አስፍሯል።
አቶ ሥንታየሁ እንደ ዜጋ ህክምና የማግኘት መብቱ በማናቸውም ሁኔታ ውስጥ ሊጠበቅላቸው ይገባል ያለው ፓርቲው፣ ነገር ግን ይህ መብታቸው የተነፈገ ስለሆነና ህመማቸው ከቀን ወደ ቀን እየበረታ ስለሆነ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ህክምና የማግኘት መብታቸው እንዲጠበቅላቸው የበኩሉን ድጋፍ እንዲያገኙ እንዲደረግ ጠይቋል።
አቶ ሥንታየሁ ቸኮል ከባልደራስ ሊቀመንበር አቶ እስክንድር ነጋና ሌሎች የፓርቲው ሰዎች ጋር ከአንድ ዓመት ለተሻገረ ጊዜ በእስር ላይ መሆናቸው ይታወቃል።