Sunday, September 22, 2024
spot_img

ኦብነግ የወይዘሮ ፊልሳን አብዱላሂን ከኃላፊነት የመልቀቅ ውሳኔ አሞገሠ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ መስከረም 18፣ 2014 ― ከነገ በስትያ በሶማሌ ክልል ከሚካሄደው ምርጫ ቀድሞ ራሱን ማግለሉን ያስታወቀው የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር፣ የሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ፊልሳን ዐብዱላሂ መሐመድ ኃላፊነታቸውን ለመልቀቅ ያሳለፉትን ውሳኔ አሞግሶ መግለጫ አውጥቷል፡፡

የወይዘሮ ፊልሳን ዐብዱላሂን ውሳኔ ‹‹ድፍረት የተሞላበት›› ያለው ኦብነግ፣ ለዓመታት ቆይቷል ያለው የሶማሌ ሕዝቦች መገፋት ያበቃል በሚል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ምክትላቸው ደመቀ መኮንን ማረጋገጫ ተሰጥቶ የነበረ ቢሆንም፣ አሁንም ይህን የመቀየር ፖለቲካዊ ፍላጎት እንደሌለ አሳውቋል፡፡

ግንባሩ የሶማሌ ሕዝቦች ይህ እንዲቀጥል ፍላጎት እንደሌላቸውም በመግለጫው ላይ አስፍሯል፡፡

በሌላ በኩል የሶማሌ ክልል የሚመራው የክልሉ አስተዳደር ባወጣው መግለጫ የሶማሌ ክልል ላለፉት 50 ዓመታት ከጦርነት፣ አመጽ፣ መፈናቀል፣ አስገድዶ መድፈር እና ድርቅ ጋር ተያይዞ ቢነሳም፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ግን ሰላም እንደሰፈነበት አሳውቋል፡፡

በብሔራዊ ደረጃም ቢሆን የሶማሌ ውክልና መጨመሩን ያስታወቀው የክልሉ መንግስት፣ የክልሉ ሁኔታ ይህን ቢያመለክትም በጦርነት ለሚነግዱ ግን አሁንም የሶማሌ ሕዝብ እንደተገለለ ነው ሲል ገልጧል፡፡ አያይዞም ይህን የሚያደርጉ አካላት ለሶማሌ ሕዝብ ሳይሆን ለራሳቸው ጥቅም የቆሙ ናቸው ብሏቸዋል፡፡ ‹‹የከሸፉ›› ያላቸው ፖለቲከኞችም ለሶማሌ ሕዝብ ሊናገሩለት አይችሉም ነው ያለው፡፡

የክልሉ መንግስት በመግለጫው ማሳረጊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እያደረጉት ላለው የሪፎርም አጀንዳ በድጋሚ ድጋፉን ገልጧል፡፡

በትላናትናው እለት የሥራ የመልቀቂያ ደብዳሜ ማስገባታቸውን ያስታወቁትና ውሳኔያቸው በኦብነግ የተሞገሱት ፊልሳን ዐብዱላሂ፣ በደብዳቤያቸው ላይ ከሥራቸው ለመልቀቅ ምክንያታቸውን በግልጽ ባያስቀምጡም፤ ‹‹ከእሴቶቼና ከታማኝነቴ ጋር ተቃራኒ የሆኑና ሥነ ምግባሬን ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ ነገሮች፤ እንዲሁም እነዚህን እምነቶች መካድ የራሴንና የዜጎቻችንን እምነት መጣስ በመሆኑ ነው›› ብለው ነበር፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img