– ሲጠበቅ የነበረው የቀድሞው ‹‹የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስቴር›› እንደማይመለስ ሲነገር፣ ሙፈሪሃት የሚመሩት ‹‹ሰላም ሚኒስቴር›› የሥም ለውጥ ያደርጋል
አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ መስከረም 18፣ 2014 ― በመጪው ሰኞ መስከረም 24 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይቋቋማል ተብሎ በሚጠበቀው አዲሱ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቶቹ አወቃቀርና ስያሜ ላይ መጠነኛ ለውጥ አድርጎ የሚኒስትር መስሪያ ቤቶች ቁጥር ከ19 ወደ 21 ከፍ እንደሚል ተሰምቷል።
በአዲሱ መንግስት ከተጣመሩትና የአደረጃጀት ለውጥ ከሚያደርጉት ውጭ ቁጥሩን ከፍ ያደረጉት፣ ወደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትነት የመጡት ሁለት ተቋማት ፍትሕ ሚኒስቴር እና ቀድሞ ኮሚሽን የነበረው የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ናቸው።
እነዚህን የፌደራል መንግሥት የአስፈጻሚ አካላት አደረጃጀት ገምግሞ የመከለሱን ሥራ በዋናነት የመራው የፕላንና ልማት ኮሚሽን ሲሆን፣ ሒደቱ ከዓመት በላይ መፍጀቱም ተነግሯል፡፡
በአዲሱ አደረጃጀት ስምንት ቁልፍ የጸጥታና የደኅንነት ተቋማትን የመምራትና የመቆጠጠር ስልጣን የተሰጠው ‹‹ሰላም ሚኒስቴር›› የስም ለውጥ አድርጎ ‹‹የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር›› ተብሎ እንዲቀየር ሐሳብ ቀርቧል። ይህን ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ባለፉት ጊዜያት የመሩት ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል በቦታቸው ይቀጥላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
‹‹የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር›› ስያሜውን ‹‹የሥርዓተ ፆታና ማኅበራዊ ጉዳይ›› በሚል ይቀይራል። ሚኒስትሯ ፊልሰን አብዱላሂ የሥራ መልቀቂያ ማስገባታቸውን ተከትሎ፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይፈርሳል/ይታጠፋል የሚል መረጃ ቢሰራጭም፣ ዋዜማ ራድዮ እንደዘገበው ከሆነ መሥሪያ ቤቱ ከውስጣዊ የአደረጃጀት ለውጥ ከማድረግ በዘለለ ባለበት ይቀጥላል፡፡
በሌላ በኩል “የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ” ተብሎ ይጠራ የነበረው መሥሪያ ቤት፣ በቀድሞ ሥሙ የፍትሕ ሚኒስቴር ይጠረል። ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በሚኒስትር ማዕረግ በሹመታቸው እንደሚቀጥሉ ዘገባው አመልክቷል። አሁን በኮሚሽንነት ያለው ፕላንና ልማት፣ ወደ ሚኒስቴርነት ከፍ ሲል፣ በቅርብ የጸደቀውን የ10 ዓመት መሪ እቅድ በማዘጋጅት የመሪነት ሚና የተጫወቱት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ባሉበት እንደሚቀጥሉ ተገምቷል።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን ‹‹የቱሪዝም፣ ስነ ጥበብና ባህል ሚኒስቴር›› በሚል የሚያዋቅረው ለውጥ፣ ‹‹ንግድና ኢንዱስትሪን›› ‹‹የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር›› ወደሚል አገር ዘለል ሚና ወዳለው ተቋም አሳድጎ ኢንዱስትሪን ከኢንተርፕራይዝ ጋራ አጣምሮታል። የከተማ ልማት ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣ ገጠርንም እንዲያካትት ተደርጎ ‹‹የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር›› ተብሎ ይዋቀራል ተብሏል።
ለውጡን ተከትሎ የፈረሰው የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ በድጋሚ ሊቋቋም ይችላል የሚል የቀደመ ግምት ቢሰጥም፣ አዲሱ ዕቅድ ሳያካትተው ቀርቷል ነው የተባለው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰኞ በፓርላማው ፊት ያቀርቡታል ተብሎ የሚጠበቀው ቀዳሚ የአስፈጻሚ መስሪያ ቤቶቻቸው ዝርዝር የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር (የሰላም ሚኒስቴር)የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የመከላከያ ሚኒስቴር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣ የኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የቱሪዝም፣ ስነ ጥበብና ባህል ሚኒስቴር፣ የማዕድን ሚኒስቴር፣ የሠራተኛ፣ ሥራ ፈጠራና ክህሎት ልማት ሚኒስቴር፣ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ፣ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር፣ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር፣ የከተማ-ገጠር ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣ የውሃ፣ አካባቢና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ሚኒስቴር፣ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የጤና ሚኒስቴር፣ የሥርዓተ ፆታና ማሕበራዊ ጉዳይ እና የፍትህ ሚኒስቴር ይሆናል ተብሎ ተጠብቋል፡፡
በሰኔ ወር 2013 በተካሄደው ምርጫ ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ማሸነፉን ምርጫ ቦርድ ማሳወቁ አይዘነጋም፡፡