አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ መስከረም 15፣ 2014 ― በመንግሥት በአሸባሪነት የፈረጀው የሕወሃት ሃይል ይገኝባቸዋል በተባሉት በደቡብ ወሎ ዞን የደላንታ ወረዳ ቀበሌዎች ውስጥ አሳሳቢ ሰብአዊ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ተፈናቅለው በወረዳው ዋና ከተማ ወገልጤና የሚገኙ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡
ከጳጉሜ 5 ጀምሮ፣ ወደ ደላንታ በመግባት አራት የሚጠጉ ቀበሌዎች በመግባቱ ወደ 10 ሺሕ ሰዎች መፈናቀላቸውን የአሜሪካ ድምጽ ዘግቧል፡፡ በነዚህ ስፍራዎች የሕወሃት ሃይል መግባቱን ደቡብ ወሎ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሰኢድ መሐመድ አረጋግጠዋል፡፡
ተፈናቅለው ወደ ሌሎች ስፍራዎች ያቀኑ ነዋሪዎች አካባቢውን የተቆጣጠረው ሃይል ከብቶችን እንደሚያርድ እና መሠረተ ልማት ማውደሙን ተናግረዋል፡፡
ተፈናቅለው በወገልጤና ከተማ የተጠለሉ የወረዳው ነዋሪዎች እስካሁን ያገኙት ምንም ዓይነት የዕለት ድጋፍ አለመኖሩን አመልክተዋል።
የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባባሪያ ጽ/ቤት በበኩሉ የደረሰው መረጃ ያለመኖሩን ገልጾ ከሚመለከተው አካል ዝርዝር እንደደረሰው ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጧል፡፡