አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ መስከረም 15፣ 2014 ― ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖም ለሁለተኛ ዙር የዓለም ጤና ድርጅትን በዋና ኃላፊነት እንዲመሩ የኬንያን መንግሥት ድጋፍ አግኝተዋል፡፡
ይህንኑ የኬንያው ጤና ሚንስትር ባለሥልጣን የሆኑት ማሻሪ ካማው በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል፡፡
የኬንያ መንግሥት ለዶ/ር ቴድሮስ ሁለተኛ ዙር መመረጥ ድጋፉን ይስጥ እንጂ፣ አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ረቡዕ እለት በተገኙበት ጋዜጣዊ መግለጫ ተሳትፏቸውን እንዲረጋግጡለት ቢጠይቅም መልስ ሳይሰጡት አልፈዋል፡፡
የዶክተር ቴድሮስ የዓለም ጤና ድርጅት እጩነትን በተመለከተ በዚህ ሳምንት የአውሮፓ ኅብረት አገራት የሆኑት ፈረንሳይ እና ጀርመንን ጨምሮ ሌሎችም የኅብረቱ አባል አገራት ድጋፋቸውን መስጠታቸው መነገሩ ይታወሳል፡፡
ያለፉትን አምስት ዓመታት የዓለም ጤና ድርጅት በአለቃነት የመሩት የቀድሞው የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስትሩ ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ከተቀሰቀሰ ወዲህ የዓለም አቀፍ ተልዕኮ ዕድላቸውን ተጠቅመው የሥራ አስፈጻሚ አባል የነበሩበት ሕወሓትን ለመርዳት ጥረት ማድረጋቸውን በማንሳት በፌዴራል መንግስት ባለስልጣናት ይተቻሉ፡፡