አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ መስከረም 15፣ 2014 ― የሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በአገሪቱ ውስጥ በተፈጠረው ሁከት ተጠርጥረው ታስረው በመሃል ተፈተው የነበሩ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ባለስልጣናት የታሰሩበትን ቦታ እንደማያውቁ ቤተሰቦቻቸው ገልጸዋል፡፡
እስረኞቹ በቅርብ ጊዜያት ታስረው ከቆዩበት ገላን ፖሊስ ጣቢያ ከረቡዕ አመሻሽ ጀምሮ ወዴት እንደተወሰዱ እስካሁን የምናውቀው ነገር የለም ሲሉ ለዶይቸ ቬለ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
የት እንዳሉ አልታወቀም የተባሉት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አመራር አባላት ኮለኔል ገመቹ አያና፣ ሚካኤል ቦረን፣ ገዳ ኦልጅራ፣ ዋቆ ኖሌ፣ ገዳ ገቢሳ፣ ኢብሳ ጋቢሳ፣ ዳዊት አብደታ፣ ጉርሙ አያና እና ለሚ ቤኛ ናቸው፡፡
እስረኞቹ ከዚህ ቀደም በፍርድ ቤት በተለያየ ጊዜ ነጻ ተብለው በድጋሚ የታሰሩ ናቸው ያሉት ጠበቃቸው አቶ ቱሊ ባይሳ፣ እስሩን የሚፈጽመው የኦሮሚያ ፖሊስ እና ልዩ ኃይል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም ሌላኛው የኦነግ አመራር አቶ አብዲ ረጋሳ ሰኔ 17፣ 2013 ከእስር ተለቀው አንድ ኪሎ ሜትር ያህል እንደተጓዙ በፖሊስ ከተወሰዱ በኋላ የት እንዳሉ አይታወቅም ብለዋል፡፡
ከሰሞኑ የት እንደተወሰዱ አልታወቀም የተባሉ የኦነግ አመራር አባሎችን በተመለከተ የፓርቲው አባል አቶ ለሚ ገመቹ ማክሰኞ እለት ጎብኝተዋቸው የነበረ መሆኑን አስታውሰው፣ ከመሃላቸው የሚታመሙ መኖራቸውንም መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን የሰጠው ምላሽ የለም፡፡