አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ መስከረም 14፣ 2014 ― የኮቪድ-19 ሕሙማንን ተቀብሎ ህክምና የሚሰጠው ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል በኮቪድ-19 ታካሚሞች እየሞላ እንደሚገኝ የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ያሬድ አግደው ገልጸዋል፡፡
የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ያሬድ፣ ኮቪድ-19 ኢትዮጵያ መግባቱ ከተገለጸ ጀምሮ ሆስፒታላቸው በቫይረሱ የተያዙ ህሙማንን ሲያክም የቆየ መሆኑን አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሕሙማን ወደ ሆስፒታሉ እየገቡ እንደሆነ ተናግረዋል።
‹‹ከአንድ ወር ከ15 ቀን ወዲህ የጽኑ ሕሙማን ክፍላችን ሙሉ ነው፤ የተቀሩት አልጋዎችም እየሞሉ ይገኛሉ›› ሲሉ የወቅቱን የሆስፒታሉን ሁኔታ ገልጸዋል፡፡
ሆስፒታሉ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ወደ 5ሺህ የሚጠጉ ታማሚዎችን ተቀብሎ ማከሙን የሚናገሩት ዶ/ር ያሬድ፤ በአሁኑ ወቅት በሆስፒታሉ ወደ 200 የሚጠጉ ሕሙማን የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሆነ ይናገራሉ።
ዶ/ር ያሬድ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ለመጨመሩ ዋናው ምክንያት ዴልታ የተሰኘው የኮቪድ ዝርያ በኢትዮጵያ መገኘቱ እንደሆነም መናገራቸውን የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል።
በተመሳሳይ ከትናንት በሰቲያ የጤና ሚንስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በኮቪድ-19 ምክንያት በጽኑ የሚታመሙ እና ህይወታቸው የሚያልፍ ሰዎች ቁጥር አሻቅቧል ብለው ነበር።
ዶ/ር ያሬድ፤ በቅርቡ በኢትዮጵያ እንደተከሰተ የተገለጸው ዴልታ ቫይረስ ከፍተኛ ከሰው ወደ ሰው የመተላለፍ አቅም ያለውና የሚያስከትለውም ሕመም የከበደ መሆኑን በማስታወሰ ሕብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል።
ከጤና ሚንስቴር የተገኘው ዕለታዊ የኮቪድ-19 አሃዝ እንደሚያመለክተው ባለፉት ሦስት ቀናት 127 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡