Sunday, September 22, 2024
spot_img

ኦፌኮ በአመራር አባላቱ መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ሕልውናው አደጋ ላይ ወድቋል ተባለ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ መስከረም 12፣ 2014 ― የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራርሮች መካከል እየተካረረ የመጣው ልዩነት የፓርቲውን ቀጣይነት አደጋ ላይ መጣሉን ዋዜማ ራድዮ ዘግቧል፡፡

ኦፌኮ ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ጋር ስትራቴጂካዊ ጥምረት መፍጠሩን ተከትሎ እየበረታ የመጣው የፓርቲ አባላት አለመግባባት በቅርቡ ኦፌኮ ከኦነግ ‹‹የኦሮሞ የሽግግር መንግስት›› መስርተናል በሚል ያወጡት መግለጫ የድርጅቱን አንዳንድ አመራሮች ከሀላፊነት አስከመልቀቅ እንዳደረሳቸው ዘገባው ያመለክታል፡፡

በቅርቡ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) እና በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ከምርጫ ራሳቸውን ለማግለል መወሰናቸውን ተከትሎ “የኦሮሚያ የሽግግር መንግስትን” ማቋቋማቸውን የሚጠቅስ መግለጫን ማውጣታቸው በፕሮፌሰር መረራ ጉዲና የሚመራው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አባላት መካከል ቅሬታ ማስከተሉንና ችግሩን ለመፍታት ከድርጅቱ ሊቀመንበር በኩል እምብዛም ፍላጎት አለመታየቱም ነው የተገለጸው፡፡

ዘገባው ስማቸውን ያልጠቀሳቸው የሥራ አስፈጻሚ አባል መሆናቸው የተገለጸ ሰው በኦፌኮ ስም ግዙፍ ትርጉም ያለው መግለጫ ሲወጣ በጉዳዩ ላይ ምንም አይነት ምክክር እንዳልተደረገ እና መግለጫውን ከህዝብ ጋር በሚድያ መስማታቸው ተጠቁሟል፡፡

ጥምረቱን በተመለከተ አንዳንድ የፓርቲው አባላት በተጠየቁባቸው መገናኛ ብዙሀን መግለጫው የኦፌኮ አቋም አለመሆኑን ለህዝብ ለማስረዳት መሞከራቸውንና የጋራ መግለጫ ለማውጣት ግን የጋራ ስብሰባ ማድረግ ባለመቻሉ እስካሁን እውነቱን ለህዝብ ለማድረስ አልቻልንም ማለታቸው ተመላክቷል፡፡

በተመሳሳይ ሥማቸው ያልተጠቀሰ ሌላኛው የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እንደሆኑ የተገለጹ ሰው ነግረውኛል ያለው ራድዮው፣ ኦፌኮ ከዳውድ ኢብሳ ኦነግ ጋር “የኦሮሞ የሽግግር መንግስት” ስለመቋቋሙ የወጣውን መግለጫ በጽሑፍ እንዳይስተባበል የከለከሉት የፓርቲው ሊቀ መንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና መሆናቸውንና የከለከሉበት ምክንያትም ግልጽ አልሆነም፡፡ ነገር ግን መግለጫው በመውጣቱ እና ሊስተባበል ባለመቻሉ መግለጫው የእኛ አቋም አይደለም በሚል የለቀቁ የቆዩ የፓርቲ አባላት መኖራቸውም ተጠቁሟል፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ አመራር አባላት መካከል በትልልቅ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሳይቀር ልዩነት እየታየ ነው የተባለ ሲሆን፣ ልዩነቶች ጎልተው መታየት የጀመሩት አሁን በእስር ላይ ሆነው የሕግ ጉዳያቸውን እየተከታተሉ የሚገኙት አቶ ጃዋር መሐመድ ፓርቲውን ከተቀላቀሉ ወዲህ እንደሆነ ዘገባው አመልክቷል፡፡

በ2012 አጠቃላይ ምርጫ መደረግ አለበት ካልተካሄደም ከመስከረም 30፣ 2013 በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው መንግስት ህጋዊነት የለውም የሚል አቋም በጃዋር መሐመድ እና በሌሎች የኦፌኮ አባላት ይንጸባረቅ ነበር። ነገር ግን በዚሁ ፓርቲ ውስጥ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ መራዘሙን እና ምርጫው እስኪደረግ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግስት ህጋዊ ሆኖ መቀጠሉን የሚደግፉ ነበሩ ነው የተባለው።

በትግራይ ያለው ጦርነት ከመጀመሩ አስቀድሞ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አባላት ሕወሓት ወደ መቀሌ ጥሪ ሲያደረግላቸው ወደዚያው መጓዛቸውን የሚቃወሙ አመራሮች ነበሩ ነው የተባለው፡፡ አሁን በእስር ላይ ያሉት የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ እና አቶ ሙላቱ ገመቹ ሕወሓት ጥሪ ሲያቀርብላችው መቀሌ ተገኝተው በስብሰባዎች ተሳትፈዋል። በመቀሌ ሕወሓት በሚጠራቸው ስብሰባዎች የሚንጸባረቁ ሀሳቦች ተገቢ አለመሆናቸውን በማንሳት ኦፌኮን ወክለው የሚሳተፉትን ከፍተኛ አመራሮች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ እንዲያደርጓቸው ለሊቀመንበሩ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ጥያቄን ያቀረቡ የፓርቲው አመራሮች ቢኖሩም፣ ፕሮፌሰር መረራ ጉዳዩን ቸል ማለት እንደመረጡ ነው በዘገባው የተመላከተው።

የፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ለችግሮች ምላሽ ለመስጠት አለመፈለግና የድርጅቱ አባላትን ጥያቄዎች በውይይት ለመፍታት አለመሞከር አንዳንድ አባላት ድርጅቱን ለቀው እንዲወጡ እያደረገ ይገኛል ተብሏል።

በጉዳዩ ላይ አሁን በሰሜን አሜሪካ የፖለቲካ ድጋፍ ለማሰባሰብ በዘመቻ ላይ የሚገኙት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና የሰጡት ምላሽ የለም፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img