Monday, September 23, 2024
spot_img

በራያ ቆቦ አካባቢ የሕወሓት ታጣቂዎች ቤት ለቤት እየዞሩ ፈጽመውታል በተባለ ጥቃት በርካቶችን መግደላቸው ተዘገበ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ መስከረም 11፣ 2014 ― የሕወሓት ታጣቂዎች ራያ ቆቦ አካባቢ ባሉ ነዋሪዎች ላይ ከአንድ ሳምንት በፊት በፈጸሙት ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ቢቢሲ ከስፍራው ሸሽተው የወጡ ነዋሪዎች ነግረውኛል ብሎ ዘግቧል፡፡

ነዋሪዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመ ነው ያሉት ጥቃት የከባድ መሳሪያ ድብደባና ቤት ለቤት በተደረገ አሰሳ መሆኑን ጠቅሰው፤ በርካቶች መሞታቸውን ነገር ግን ስለደረሰው ጉዳት አሃዝ በትክክል ለማወቅ አስቸጋሪ መሆኑን መናገራቸው ነው የተመላከተው፡፡

ቢቢሲ አናገርኳቸው ያላቸው ግለሰቦች ጥቃቱ ሲፈጸም በስፍራው እንደነበሩና በአሁኑ ወቅት ደሴ ከተማ በሚገኝ የተፈናቃዮች መጠለያ ውስጥ እንደሚገኙም ነው ያስነበበው፡፡

በዘገባው ቃላቸው ከሰጡ ሰዎች መካከል አንደኛው የሕወሓት ታጣቂዎች ‹‹ከገቡ ጊዜ ጀምሮ የመንግሥት እና የግለሰብ ቤትን ከመዝረፍ እና ከማውደም በዘለለ ለአንድ ወር ያህል በሰው ላይ ብዙም እንግልት አልደረሰም ነበር›› ያለ ሲሆን፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎት በመቋረጡ ነዋሪው እህል አስፈጭቶ ለመመገብ ተቸግሮ ስለነበር ቆቦ ጊራና ከሚባለው ፕሮጀክት ጀኔሬተር በማስነሳት ወፍጮዎች አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ ሰዉን መመገብ ጀምረው እንደነበርም አስታውሷል፡፡

እንደ ዐይን እማኙ ይህ አገልግሎት የቆየው ለአምስት ቀናት ብቻ ነበር። ከአምስት ቀናት በኋላ ወደ ቆቦ ተቀይሮ የመጣው የታጣቂዎቹ አመራር ‹‹ጀኔሬተሩን ነቅሎ›› መውሰዱን ገልጧል፡፡ አያይዞም ‹‹የተቀየረው የህወሓት ኃይል አመራርም አርብ መጥቶ ቅዳሜ ነሐሴ 22፣ 2013 አራሞ እና ገደመዩ ወደሚባሉ የገጠር ቀበሌዎች በማምራት ‹‹መሳሪያ አምጡ›› በማለት ተኩስ ከፈቱ በማለት አካባቢው በህወሓት ቁጥጥር ሥር ከዋለ ከአንድ ወር በኋላ በራያ ቆቦ ዳግም ጦርነት ተቀስቅሷል ነው ያለው፡፡

በዚህ ጥቃትም መሳሪያ አምጣ በማለት ካሳ ከበደ የሚባል የአራሞ ቀበሌ ነዋሪ መገደሉንና አጠገቡ የነበረው የ13 ዓመት ታዳጊም አባቴን ብሎ ወደአባቱ አስከሬን ሲቀርብ መገደሉን የዐይን እማኙ አክለዋል፡፡

ቀጥለውም ‹‹በተመሳሳይ ግድያ ሌሎች አርሶ አደሮች ላይም መሳሪያ አምጡ በሚል ሰበብ ተፈጽሟል›› የሚሉት ነዋሪው፣ ‹‹እንደዚህ መግደል ሲጀምሩ አርሶ አደሩ ራሱን ለመከላከል መልስ መስጠት ጀመረ›› ሲሉ ሁኔታውን አስታውሰዋል፡፡

በእዚሁ ዕለት (ነሐሴ 22/2013) ጥቃት የተከፈተባቸው የገጠር ቀበሌ አርሶ አደሮች ራሳቸውን እያጠናከሩ እና ኃይል እየጨመሩ ‹‹የህወሓት ታጣቂዎችን ከገጠሩ አካባቢ አስወጥተው ወደ ከተማው [ቆቦ]›› ቢያደርሷቸውም አርሶ አደሮቹ ወደ ከተማው ሳይገቡ ወደ መጡበት እንደተመለሱም ሌላኛው የዐይን እማኝ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀን በኋላ ለአምስት ቀናት በገጠሩም ሆነ በከተማው ተጨማሪ ጥቃት አለመፈጸሙን ያስታወሱት ነዋሪዎቹ፣ በአምስተኛው ቀን ማለትም ነሐሴ 27፣2013 ግን የህወሓት ኃይሎች የቆቦ ከተማን ከብበው ‹‹መሳሪያ አምጡ›› እያሉ ነዋሪውን ሲደበድቡ መሳሪያ ያለው መስጠቱንና የሌለው ደግሞ የለኝም በማለቱ ከፍተኛ ድብደባ ይፈጽሙበት ነበር ነው የሚሉት፡፡

ሦስተኛውና ከፍተኛ የሰው ሕይወት ያለቀበት ጥቃት የተፈጸመው በጳጉሜ አራት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአርሶ አደሮቹ ታጣቂዎቹን መግጠም ተከትሎ የሕወሃት ታጣቂዎች ፈጽመውታል በተባለው የበቀል ጥቃት ‹‹ጦርነቱን ፈርቶ የተቀመጠውን ሰው ሁሉ ቤት ለቤት እየዞሩ፣ ከዚያ ውጪ በእርሻ ቦታዎች አረም ሲያርም ውሎ ወደ ቤቱ የሚገባውን ሰው ሁሉ መንገድ ላይ እየጠበቁ›. መግደላቸውንም ነው የዐይን እማኞቹ የገለጹት፡፡

በጉዳዩ ላይ ጥቃቱን አድርሷል የተባለው ሕወሃትም፣ የአማራ ክልል መስተዳደርም ሆነ የፌደራል መንግሥቱ የሰጡት ማብራሪያ የለም።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img