አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ መስከረም 10፣ 2014 ― በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀውና ከፌዴራል መንግስት ጋር ጦርነት ውስጥ የሚገኘው ሕወሓት ከሰሞኑ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የፈረሙበት ማእቀብ ተፈጻሚ እንዲሆን እሠራለሁ ሲል ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የፈረሙበትና በአገሪቱ ግምጃ ቤት ተፈጻሚ እንዲሆን ያዘዙት መመሪያ በኢትዮጵያ ግጭት እንዲራዘም፣ ሰብአዊ ርዳታ እንዳይደርስ እና ተኩስ አቁም እንዳይደረግ መሰናክል በመሆን ተጠያቂ ናቸው ያሏቸው አካላት ላይ የገንዘብ ዝውውር እና የጉዞ ማዕቀብ እንዲጣል የሚያደርግ መሆኑ መነገሩ ይታወቃል፡፡
በዶክተር ደብረጺዮን ተፈርሞበት የወጣው መግለጫ፣ የመመሪያውን መፈረም ትክክለኛነት የገለጸ ሲሆን፣ መመሪያው ለማሳካት የሚያልማቸው ጉዳዮች ተፈጻሚ እንዲሆኑ በግጭቱ ተሳትፎ ያላቸውና ወንጀሎችን የፈጸሙ ግለሰቦችና ቡድኖች መለየት እንዲሁም ምርመራዎች እንዲካሄዱ እና በስሩ የታቀፉና ጥፋት ያደረሱ አካላትን ለፍትሕ ለማቅረብ እንደሚሠራም ነው ያሳወቀው፡፡
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ቀናት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በሠሜን ኢትዮጵያ ያለውን ጦርነት በተመለከተ በተሳታፊዎቹ ላይ ማዕቀብ ለመጣል የሚያስችል ትዕዛዝ መፈረማቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ግልጽ ደብዳቤ መጻፋቸውም ይታወሳል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በደብዳቤያቸው የኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ ወዳጅና የደኅንነት ስትራተጂካዊ አጋር ነች ያሏት ዩናይትድ ስቴትስ ‹‹ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሬ ላይ የምትከተለው ፖሊሲ አስገራሚ ብቻ ሳይሆን በግልጽ በሚታይ ሁኔታ ለሰብአዊነት ከመቆርቆር ያለፈ ነው›› ሲሉ ተችተዋል።
በተሳሳተ ምክንያት መላው ዓለም ዐይኑን በኢትዮጵያ ላይ ማተኮሩን በመጥፎ አጋጣሚነት ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በተመሳሳይ በአገሪቱ ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀውን ቡድን ‹‹በይፋ ተጠያቂ ለማድረግ አልቻለም›› ሲሉም ወቅሰዋል፡፡
አክለውም ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ውስጥ ካካሄደችው ሕግን የማስከበር ዘመቻ ጋር በተያያዘ በአገሪቱ ላይ እየተፈጸመ ያለው ተገቢ ያልሆነ ያሉት ይህ ጫና ‹‹አድሏዊ በሆነና መሬት ላይ ያለውን እውነታ በተቀናበራ ሁኔታ ማዛባትን መሠረት ያደረገ ነው›› ሲሉ አጣጥለውታል።
ባይደን ከሰሞኑ በፈረሙት ማዕቀብ የሚካተቱ ግለሰቦችና ባለሥልጣናት ሊገጥማቸው የሚችሉ ነገሮች ቤተሰቦቻቸው እና ልጆቻቸውንም ይመለከታል ተብሏል፡፡