አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ መስከረም 10፣ 2014 ― ከሰሜን ወሎ የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በደሴ ከተማ ቤት ተከራይተው የሚገኙ ግለሰቦች መንግሥትና በጎ አድራጊዎች በሚያደርጉት ድጋፍ ላይ አድሎ እየተፈጸመባቸው መሆኑን ነግረውኛል ብሎ አዲስ ማለዳ ጋዜጣ አስነብቧል፡፡
በድጋፍ አሰጣጡ አድሎዓዊ አሠራር አለ የሚሉት ተፈናቃዮቹ፣ በጦርነቱ በተፈናቀሉበት ወቅት ሕፃናትን ይዘው ስለነበር በፍጥነት መጠለያ እንደሚያስፈልጋቸው በመገንዘባቸው ለጊዜው ቤት ቢከራዩም፣ አሁን ያላቸውን ገንዘብ ስለጨረሱ ለሌሎች ተፈናቃዮች የሚደረገውን ድጋፉ እያገኙ አለመሆናቸውን ነው የጠቆሙት።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ የሚናገሩት የእርዳታ ድጋፍ የሚያገኙት በከተማው ባሉ የተለያዩ መጠለያዎች የሚገኙ ሰዎች በመሆናቸው ወደ መጠለያዎቹ መቀላቀል ቢፈልጉም መጠለያዎቹ በመሙላታቸው መጠጋት እንዳልቻሉና ከመንግሥትም ሆነ ከበጎ አድራጊዎች የሚመጣውን ድጋፍ እንደሌሎች ተፈናቃዮች እያገኙ አለመሆናቸውን ነው።
የመጠለያ ቦታው ቢሞላም በተከራየንበት ሆነን ድጋፍ ሊሰጠን ይገባል የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ ከየአካባቢው የተፈናቀሉትን የእርዳታው ተካፋይ ለማድረግ የሚመዘግቡ አካላት ዘንድ ሔደው ቢመዘገቡም፣ በመጠለያ ያሉት ተፈናቃዮች እንጂ እነርሱ እስካሁን እርዳታ እንዳላገኙ አብራርተዋል።
ተፈናቃዮቹ እስካሁን ድረስ ከአንዳንድ ቤተሰቦቻቸው በሚላክላቸው የብር ድጋፍ ቤት ተከራይተውና የዕለት ምግባቸውን ገዝተው ሲኖሩ የቆዩ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ምንም አይነት የድጋፍ ምንጪ ስለሌላቸው ከሕፃናት ልጆቻቸው ጋር የመጠለያና የምግብ ዕጥረት እንደገጠማቸው ነው የተነገረው፡፡
ጋዜጣው አለ የተባለውን “አድሎዓዊ” አሠራር ከደሴ ከተማ ምክትል ከንቲባ ሰዒድ ዩሱፍ ለማረጋገጥ ችያለሁ ብሏል፡፡ እንደ ከንቲባው በደሴ ከተማ ለሚገኙ ተፈናቃዮች ከሦስትና አራት ጊዜ በላይ ዕርዳታ የተደረገ ሲሆን፣ በየአካባቢው ያሉት መዝጋቢዎች የሚያውቋቸውን ብቻ ደጋግመው ስለሚመዘግቡ የዕርዳታ ክፍፍሉ አስቸጋሪ እንደሆነባቸውና በተለይም ከመርሳና ከቆቦ ለመጡት ተፈናቃዮች ዕርዳታ በሚደረግበት ወቅት ችግር ገጥሟቸዋል፡፡
በተጨማሪም በደሴ ከተማ ተጠልለውና ተከራይተው የሚኖሩትን ጨምሮ ከሁለት መቶ 80 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች በመኖራቸውና በየዕለቱ ቁጥራቸው እየጨመረ በመምጣቱ ትርምስ ስላለ እርዳታውን በትክክል ለማዳረስ ተቸግረናል ነው ያሉት፡፡
ምክትል ከንቲባው አክለውም መዝጋቢዎች እንደፈለጉ መዝግበው ስለሚያቀርቡ እና በተፈናቃዮች መካከል መተዛዘን ስለሌለ አቅም የሌላቸው አዛውንቶችም ጭምር ዕርዳታ ሳያገኙ እንደሚቀሩ ነው የጠቆሙት። ምክትል ከንቲባው ችግሩን ለመፍታት ከሚመለከታቸው ጋር ውይይት እያደረጉ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን፣ በዚህ ወቅት ከምንም በላይ መተዛዘን ያስፈልጋል ማለታቸውም ተመላክቷል፡፡