Sunday, September 22, 2024
spot_img

ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት መስመር ሲያልፉ ተጠያቂ የሚያደርግ መመሪያ ተዘጋጀ

አምባ ዲጂታል፣ እሑድ መስከረም 9፣ 2014 ― ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት የመንግሥትን ፖሊሲና ውሳኔ በአደባባይ ሲጥሱ፣ ስጦታ ሳያሳውቁ ሲቀበሉ፣ ያለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከወከላቸው ተቋማት ፈቃድ ውጪ ጉብኝት ሲያደርጉ፣ እንዲሁም የተሳሳተ መረጃ ለፓርላማው፣ ለመንግሥት ወይም ለሚዲያ ሲሰጡ ቢገኙ ተጠያቂ የሚያደርግ ረቂቅ ሕግ መዘጋጀቱ ታውቋል።

ረቂቅ የሥነ ምግባር ደንቡ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ወይም የልማት ድርጅቶችን በኃላፊነት የሚመሩ ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ ኮሚሽነሮች፣ ምክትል ኮሚሽነሮች፣ ዋና ዳይሬክተሮች፣ ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች፣ ዋና ሥራ አስኪያጆችና ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጆችን የሚመለከት መሆኑን ሪፖርተር ጋዜጣ ሰነዱን ጠቅሶ ዘግቧል።

በፌዴራል የሥነ ምግባር ፀረ ሙስና ኮሚሽን በኩል ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊላክ የመጨረሻ ሒደት ላይ የሚገኘው ይህ ረቂቅ ሕግ፣ በተመሳሳይ የኃላፊነት ደረጃ የተሰየሙ ሌሎች የሥራ ኃላፊዎችን፣ እንዲሁም የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባዎችን፣ ምክትል ከንቲባዎችን፣ የቢሮ ኃላፊዎችንና ሌሎች በተመሳሳይ ደረጃ የተሰየሙ የመንግሥት ኃላፊዎችን እንደሚያካትት ተጠቁሟል፡፡

ከላይ የተጠቀሱት የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች በአደባባይ ለሕዝብ ቃል የተገባን ያለ በቂ ምክንያት ካጠፉ፣ በታማኝነት ጉድለት ምክንያት የተፈጠሩ ስህተቶችን በወቅቱ ካላስተካከሉና ይቅርታ ካልጠየቁ፣ ሆን ብለው ሕጋዊ ውሳኔን ካደናቀፉ ወይም ካዘገዩ፣ በሕግ ሚስጥር ናቸው ተብለው የተለዩ ጉዳዮች ተጠብቀው እንዲያዙ ካላደረጉ በሕግ የሚጠየቁበት አሠራር ዘርግቷል፡፡

በተጨማሪም በሥራ ላይም ሆነ ወይም ሥራን ለቆ ሚስጥር አሳልፎ መስጠት፣ የመንግሥት ፖሊሲ በሚቀረፅበት ወይም ውሳኔ በሚሰጥበት ጊዜ የተወሰኑ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ያላግባብ የተለየ ጥቅም የሚያገኙበት ሁኔታ ማመቻቸት፣ ኃላፊው የግል የኢንቨስትመንቱንና የግል ድርጅቱን በወኪል ማሠራት፣ ካፒታልና ትርፍን በማያዝበት የባንክ ሒሳብ ማስቀመጥ፣ ኃላፊነቱን ከለቀቀ በኋላ ቀድሞ ይሠራበት በነበረው መሥሪያ ቤት ውስጥ ከሁለት ዓመት በፊት በአማካሪነት በውል አዘጋጅነት ወይም መሥሪያ ቤቱ በሚያወጣው ጨረታ እንዳይሳተፍ ይከለክላል፡፡

ረቂቅ የሥነ ምግባር ደንቡ ማንኛውም የመንግሥት ተሿሚ የተጠቀሱትን በርካታ ዓይነት ድንጋጌዎች ጥሶ ቢገኝ ለጥፋቱ ይቅርታ እንዲጠይቅ፣ በራሱ ፈቃድ የሥራ ስንብት እንዲጠይቅና ከኃላፊነት እንዲሰናበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ የሚሰጡ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪ ግን አስተዳደራዊና በማናቸውም ዓይነት የወንጀል ወይም የፍትሐ ብሔር ሕግ ተጠያቂ እንደሚሆን ያብራራል፡፡

በኮሚሽኑ የሀብት ማስመዝገብና ማረጋገጥ ዳይሬክተር አቶ መስፍን በላይነህ እንዳስታወቁት፣ ከዚህ ቀደም በነበሩ አሠራሮች ሕግ ተጠያቂ የሚያደርገው የመንግሥት ሠራተኞችን እንጂ የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎችን እንዳልነበረ ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም አዲሱ ረቂቅ የሥነ ምግባር ሕግ ተዘጋጅቶ መምጣቱ፣ ባለሥልጣናቱ ተግባርና ኃላፊነታቸውን ሲያከናውኑ የወጣውን የሥነ ምግባር ደንብ ተላልፈው ሲገኙ ተጠያቂ ለማድረግና የመንግሥትና የግል ጥቅሞች እንዳይቀላቀሉ ማሰሪያና ገዥ ሕግ ይሆናል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የተዘጋጀው ረቅቅ ደንብ አዋጅ ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ እንዳለ አቶ መስፍን ተናግረዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img