Sunday, September 22, 2024
spot_img

የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ቦብ ሜንዴዝ ለተመድ የጻፉትን ደብዳቤ መንግሥት አወገዘ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ጳጉሜን 3፣ 2013 ― የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሴናተር ቦብ ሜንዴዝ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦርን በተመለከተ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የላኩትን ደብዳቤ፣ ኢትዮጵያ እንደምታወግዘው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን አስታውቀዋል፡፡

አቶ ደመቀ ከትላንት በስትያ ሰኞ ጳጉሜን 1፣ 2013 የተመድ የሰላም ማስከበር ጉዳዮች ረዳት ጸሐፊ ጃንፒዬር ላክሮይዝን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት፣ የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ከአንድ ወር በፊት ለተመድ ዋና ጸሐፊ የላኩት ደብዳቤ ኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ጦሯን በተለያዩ አገሮች በመላክ ለሰላም ያበረከተችውን አስተዋጽኦ የዘነጋ ነው ሲሉ ገልጸውታል፡፡

ሴናተር ቦብ ሜንዴዝ ከአንድ ወር በፊት ለተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ በላኩት ደብዳቤ፣ በትግራይ ክልል ጦርነት ውስጥ የተሳተፉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ከዚህ በኋላ ለሰላም አስከባሪነት እንዳይሰማሩ የሚጠይቅ ነው፡፡

የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ሰብሳቢው በደብዳቤያቸው በትግራይ ክልል ጦርነት በርካታ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በወታደሮች መፈጸማቸውን የሚጠቁሙ መረጃዎች የወጡ በመሆናቸው፣ በዚህ ክልል የተሰማራው ጦር በተመድ ሥር ሆኖ በሰላም አስከባሪነት ቢሰማራ ተመሳሳይ ጥሰት በተሰማራበት አካባቢ አለመፈጸሙን ርግጠኛ መሆን እንደማይቻል ገልጸዋው ነበር፡፡

ምንም እንኳ ኢትዮጵያ በሰላም አስከባሪነት በግንባር ቀደምትነት በተመድ ሥር እየተሳተፈች ቢሆንም፣ ከዚህ በኋላ ግን ኢትዮጵያ የምትልከው የሰላም አስከባሪ ኃይል በትግራይ ጦርነት ውስጥ የተሳተፈ መሆን አለመሆኑ ሳይጣራ ተመድ እንዳይቀበል ጠይቀውም ነበር፡፡

አቶ ደመቀ መኮንን ይህ የሴናተሩ ደብዳቤ መንግሥታቸውን እንዳሳዘነ ለተመድ የሰላም አስከባሪ ጉዳዮች ረዳት ጸሐፊ እንደገለጹላቸው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img