Friday, November 22, 2024
spot_img

የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ መምጣቸው አይቀሬ መሆኑ ተጠቆመ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ጳጉሜን 3፣ 2013 ― ለውጭ ባንኮች ዝግ ሆኖ የቆየው የኢትዮጵያ ፋይናንስ ዘርፍ በመከፈቱ የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው ስለማይቀር ባንኮች ከፊታቸው ለሚጠብቃቸው ፈታኝ ውድድር መዘጋጀት እንደሚኖርባቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ አሳስበዋል፡፡

ይህንኑ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ባለ 37 ወለል የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ የምረቃ ሥርዓት ላይ የገለጹት ዶክተር ይናገር፣ ዘርፉ ለውጭ ባንኮች መቼ ክፍት ይሆናል የሚለውን ግን አልመለሱም፡፡

ዶክተር ይናገር ባንኮቹ ከፊታቸው ሊጠብቃቸው የሚችለውን ውድድር ታሳቢ በማድረግ መንቀሳቀስ እንደሚኖርባቸው ያመለከቱ ሲሆን፣ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠልም ሆነ ከኢትዮጵያ ውጪ በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ባንኮች ለመሆን ደግሞ ባንኮች የዘመኑን ቴክኖሎጂ መታጠቅ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት ለመስጠትና መጪውን ውድድር ለመቋቋም የሁሉም ባንኮች የቦርድ አባላትና አመራሮች ለዚህ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል፡፡

በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ ባንኮች በየዓመቱ ዕድገት ለማሳየታቸው ከሚያደርጉት ጥረት ባሻገር፣ የብሔራዊ ባንክ ያልተቋረጠ ቁጥጥርና ክትትል የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ እንዳለው በመጥቀስ፣ ‹‹ብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር ያበዛል›› መባሉ ተገቢ እንዳልሆነም ጠቁመዋል፡፡

ከተለያዩ አቅጣጫዎች ‹‹የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር ያበዛል›› የሚል አስተያየትን እንደሚሰሙ ያመለከቱት ይናገር (ዶ/ር)፣ የብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር ይጠቅም ይሆናል እንጂ ጉዳት የለውም ብለዋል፡፡ አክለውም በቁጥጥሩ እንደሚቀጥልበትም ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ባንኮች አሁን ያሉበት የዕድገት ደረጃ ላይ የመድረሳቸውም ሆነ፣ በየዓመቱ ከፍተኛ ትርፍ በማግኘት የመቀጠላቸው ሚስጥር የብሔራዊ ባንክ ቁጥጥርና ክትትል ውጤት እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

‹‹በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ እንደ ሱቅ እየከሰሩ የሚዘጉ ባንኮች አሉ፤›› ያሉት ገዥው፣ ‹‹እንዲህ ያለው ታሪክ ኢትዮጵያ ውስጥ አለመታየቱ የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ያለበትን ደረጃ አመላካች ነው፤›› ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የግል ባንኮች መሥራት እንዲችሉ ከተፈቀደበት ጊዜ አንስቶ በኪሳራ የተዘጋ ባንክ እንደሌለ፣ ወደፊትም በኪሳራ የሚዘጋ ባንክ እንደማይኖር ያላቸውን ተስፋም ገልጸዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img