አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ጳጉሜን 1፣ 2013 ― የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሱዳን ካርቱም ያጓጓዝኳቸው የጦር መሳሪያዎች ሕጋዊ ናቸው ሲል ምላሽ መስጠቱን ቢቢሲ አስነብቧል፡፡
አየር መንገዱ እንዳለው ከሆነ መሳሪያዎቹ ወታደራዊ ሳይሆኑ ለአደን አገልግሎት የሚውሉ ከመሆናቸው በተጨማሪ አስፈላጊው ሕጋዊ የመጓዣ ሰነድ ያላቸው ናቸው።
የኢትዮጵያ አየር መንገዱ የሱዳን መንግሥት የዜና ወኪል የሆነው ሱና በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጓጉዘው ሱዳን የገቡት ጦር መሳሪያዎች ‹‹[በሱዳን] መንግሥት ላይ ወንጀል ለመፈጸም›› ጥቅም ላይ ሊውሉ ነበር የሚል ጥርጣሬ አለ ሲል ያወጣውን አጣጥሏል።
ሱዳን በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ካርቱም ከገቡ በኋላ ተይዘዋል ስላለቻቸው የጦር መሳሪዎች ምርመራ እያደረኩ ነው ስትል ማስታወቋ ይታወሳል።
እንደ ሱና ዘገባ ከሆነ መነሻውን ከአዲስ አበባ አድርጎ ቅዳሜ ምሽት ካርቱም ባረፈው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ውስጥ ተጭኖ የነበረ ጦር መሳሪያ በሱዳን ጉምሩክ ባለሥልጣናት ተይዟል።
ሱና የጦር መሳሪያዎቹን ጉዳይ እንዲያጣራ የተቋቋመው ኮሚቴ ጦር መሳሪያዎቹ ከሩሲያ ሞስኮ ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ በኋላ ለሁለት ዓመታት ተቀምጠው ለሱዳን መንግሥት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ በሲቪል አውሮፕላን ወደ ካርቱም እንዲጫኑ አዲስ አበባ ፈቅዳለች ማለቱን አስነብቦም ነበር።
አየር መንገዱ በበኩሉ የጦር መሳሪያዎቹ አዲስ አበባ በሚገኙ የደኅንነት ባለስልጣናት ለረዥም ጊዜ የማጣራት ሥራ ሲከናወንባቸው ቆይቷል ይላል።
አየር መንገዱ ከዚህ በተጨማሪም የመሳሪያው መጓጓዝ ሕጋዊነትን የሚያረጋግጥ ከሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የተጻፈ ደብዳቤ አለኝ ብሏል።