Wednesday, November 27, 2024
spot_img

ሱዳን ከኢትዮጵያ የተላከ በርካታ የጦር መሣሪያ በቁጥጥር ሥር አውላ ምርመራ መጀመሯን አሳወቀች

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ጳጉሜን 1፣ 2013 ― ጎረቤት አገር ሱዳን በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ካርቱም ከገቡ በኋላ ተያዙ የተባሉ የጦር መሳሪዎች ላይ ምርመራ እያደረኩ ነው ብላለች፡፡

መንግሥታዊው የሱዳን ዜና ወኪል ሱና እንደዘገበው ከኢትዮጵያ በአየር ትራንስፖርት ተጓጉዘው ሱዳን ገብተዋል ያላቸው ጦር መሳሪያዎች ‹‹[በሱዳን] መንግሥት ላይ ወንጀል ለመፈጸም›› ጥቅም ላይ ሊውሉ ነበር የሚል ጥርጣሬ አለ ብሏል።

ሱና የጦር መሳሪያዎቹን የጫነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ መነሻውን ከአዲስ አበባ አድርጎ ቅዳሜ ምሽት ካርቱም ካረፈ በኋላ በአገሪቱ ጉምሩክ ባለሥልጣናት ተይዟል በማለት ኮሚቴውን ጠቅሶ ዘግቧል።

ከዚህ በተጨማሪም በካርቱም የተያዙት ጦር መሳሪያዎች ግንቦት 2011 ከሩሲያ ሞስኮ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ናቸው ነው ያለው፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዑመር አል በሺር መንግሥትን ለማፍረስ የተቋቋመው ኮሚቴ ምርመራ እንዲያደርግ ኃላፊነት እንደተሰጠው ነው የተገለጸ ሲሆን፣ ኮሚቴው በበኩሉ ጦር መሳሪያዎች በ72 ሣጥኖች መጓጓዛቸውን እና በውስጡም ከጦር መሳሪያዎች በተጨማሪ በጨለማ መመልከት የሚያስችሉ መነጽሮች ይገኙበታል ብሏል።

አክሎም ካርቱም ገብተዋል የተባሉት ጦር መሳሪያዎች ‹‹የዲሞክራሲ ሽግግርን ለማደናቀፍ እና ወደ ሲቪል መንግሥት ሽግግር እንዳይኖር በመንግሥት ላይ ወንጀል ለመፈጸም›› ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ የሚል ግምት እንዳለውም ገልጧል፡፡

እስካሁን ድረስ በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ አየር መንገዱ በሱዳን መንግሥት ለቀረበው ክስ ምላሽ አልሰጡም።

ሬውተርስ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ዲና ሙፍቲ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡኝ ብጠይቅም ምላሽ አላገኘሁም ሲል አስነብቧል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img