አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ነሐሴ 28፣ 2013 ― የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሕይወት ያሉ የዱር እንስሳትን የማጓጉዘው በከፍተኛ ጥንቃቄ ዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ፣ ብሔራዊ ሕጎችን እና የውስጥ አሰራርን በመከተል ነው ብሏል፡፡
አየር መንገዱ ይህን ያለው ተቋሙ ለንግድ የሚውሉ የዱር እንስሳትን አስከፊ በሆነ አያያዝ ከምዕራብ አፍሪካ ወደተለያዩ መዳረሻዎች ያጓጉዛል የሚል አንድ ጥናታዊ ሪፖርት ይፋ ከሆነ በኋላ ነው።
ዎርልድ አኒማል ፕሮቴክሽን የተሰኘ ድርጅት ይፋ ባደረገው የጥናት ሪፖርት ላይ አየር መንገዱ ከዚህ ተግባሩ ተቆጥቦ ለዱር እንስሳት ተስማሚ ኩባንያ መሆን አለበት ሲል ጥሪውን አቅርቦ ነበር፡፡
አየር መንገዱ በበኩሉ እንደ ዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር አባልነቴ በሕይወት ያሉ እንስሳትን የማጓጓጉዘው ሰብዓዊ እና ሕጋዊ በሆነ መልኩ ነው ሲል የቀረበበትን ክስ ውድቅ አድርጓል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለዚህ ሪፖርት ምላሽ በሰጠበት መግለጫ ላይ የትኛውንም አይነት የዱር እንስሳት የማጓጉዘው ዓለም አቀፍ ሕግጋትን በተከተል መልኩ ነው በማለት እንስሳቱ የተጓጓዙት ሕጋዊ መንገድን ባልተከተለ ነው መባሉን አጥብቆ ተቃውሟል።
አየር መንገዱ አክሎም የዱር እንስሳትን ከማጓጓዙ በፊት ላኪው እና ተቀባዩ ሕጋዊ ፍቃድ እንዳላቸው እንዲሁም አስፈላጊ የጤና ቅድመ ሁኔታዎች መሟላታቸውን አረጋግጣለሁ ብሏል።