Sunday, September 22, 2024
spot_img

በምሥራቅ ወለጋ ታጣቂዎች ጥቃት ሰንዝረው እስረኞችን ማስመለጣቸው ተነገረ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ነሐሴ 27፣ 2013 ― በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ሳሲጋ ወረዳ ታጣቂዎች በአንድ ፖሊስ ጣቢያ ላይ በፈጸሙት ጥቃት እስረኞችን አስመልጠው በርካታ የፖሊስ አባላትን ማቁሰላቸው ተነገረ።

ቢቢሲ ከአካባቢው ነዋሪዎች እና ከሆስፒታል ምንጮች አረጋግጫለሁ ብሎ እንደዘገበው ጥቃቱ የተፈጸመው ከትላንት በስትያ ማክሰኞ ዕለት ነሐሴ 25 ነው።

ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር እያለ የሚጠራውና ከወራት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪ ድርጅትነት የተፈረጀው መንግሥት ሸኔ እያለ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ጥቃቱን ስለመፈጸሙ አስታውቋል።

በሳሲጋ ወረዳ የጋሎ ከተማ ነዋሪ የሆኑ አንድ ግለሰብ ጥቃቱን በተመለከተ እንደተናገሩት ማከሰኞ ረፋድ 3፡30 አካባቢ በከተማዋ የተኩስ ድምጽ መሰማት እንደጀመረ ገልጸዋል።

የተኩስ ልውውጡም በአካባቢው በነበሩ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና ታጣቂዎቹ መካከል መሆኑን እና ይህም እስከ እኩለ ቀን መቀጠሉን ይናገራሉ።

ታጣቂ ቡድኑ ጥቃት የፈጸመው በሳሲጋ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ ላይ ሲሆን፣ በዚህም ጥቃት እስረኞችን ማስመለጡን ነዋሪው ይናገራሉ።

“ከእስር ቤቱ ያመለጡ ስድስት ሰዎች እኔ ወደ ምሠራበት ቦታ ሸሽተው ገብተው ነበር። ክፍት በር ሲያገኙ ነው ዘልቀው የገቡት። ከዚያ በኋላ ወጥተው ሄዱ። እኔም የሥራ ቦታዬን ዘግቼ ከአካባቢው ሄድኩ” በማለት የገጠማቸውን ገልጸዋል።

የታጣቂ ቡድኑ ቃል አቀባይ በተረጋገጠው የትዊተር ገጽ ላይ ቡድኑ በሳሲጋ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ ላይ ጥቃት ስለመፈጸሙ አስፍሯል።

በዚህም ጥቃት “ከ100 በላይ የፖለቲካ እስረኞች ተለቀዋል” ብሏል።

ሆኖም የዜና ተቋሙ ሰዎች ከእስር ያመለጡ ሰዎችን ቁጥር በተመለከተ ትክክለኛ ቁጥሩን ከገለልተኛ ወገን ማጣራት አልቻልኩም ብሏል።

ጥቃቱን ተከትሎ በቁጥር ከ40 በላይ የሚሆኑ የአካባቢው የፖሊስ አባላት ላይ የተለያየ ጉዳት ደርሶባቸው ለሕክምና ወደ ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል መምጣታቸውን ከሆስፒታሉ ማረጋገጥ እንዳልተቻለ በዘገባው ተመላክቷል።

የኦሮሚያ ክልል ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ባልቻ ስለጉዳዩ ተጠይቀው “እኔ አላውቅም። በዚህ ጉዳይ ላይ መረጃ የለኝም” በማለት ዛሬ ምላሽ ሰጥተዋል ነው የተባለው።

ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር እያለ የሚጠራው እና መንግሥት “ሸኔ” የሚለው ታጣቂ ቡድን በምዕራብ ኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች በመንግሥት ባለሥልጣናት እና የጸጥታ አካላት ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ሲሰነዝር ቆይቷል።

ከጥቂት ወራት በፊት የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በዚህ ታጣቂ ቡድን 112 የፖሊስ አባላት፣ 57 የሚሊሻ አባላት እና በተለያየ ደረጃ የሚገኙ 18 ባለሥልጣናት መገደላቸውን አስታውቆ ነበር።

በተጨማሪም በአካባቢዎቹ በተለያዩ ጊዜያት በንጹሃን ነዋሪዎች ላይ በተደጋጋሚ ከተፈጸሙ የጅምላ ግድያዎች ጋር በተለያያዘ ክስ ሲቀርብበት ቆይቷል።

ከሳምንት በፊት በምስራቅ ወለጋ ኪራሙ ወረዳ ከ100 በላይ ንጹሃን ሰዎች የቡድኑ ታጣቂዎች ናቸው በተባሉ ጥቃት ፈጻሚዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣት መግለጫ አስታውቆ ነበር።

ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጣራውና መንግሥት ሸኔ የሚለው ይህ ታጣቂ ቡድን ከፌደራል መንግሥቱ ጋር በሰሜን ኢትዮጵያ ከባድ ጦርነት ውስጥ ከሚገኘው ከህወሓት ጋር በጋር ፀረ መንግሥት እንቅስቃሴ ለማድረግ መስማማቱን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img