Friday, October 18, 2024
spot_img

ጦርነት ባለባቸው አካባቢዎች የሕዝብ ለሕዝብ ውይይት እንዲደረግ ጥሪ ቀረበ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ነሐሴ 27፣ 2013 ― የኢትዮጵያ ዕርቀ ሰላም ኮሚሽን በአሁኑ ጊዜ የተከሰቱ አጠቃላይ ችግሮችን ለማብረድና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን፣ ግጭትና ጥቃት እንዲሁም ጦርነት ባለባቸው አካባቢዎች የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትና ውይይት እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ኮሚሽኑ ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ የአገር ሽማግሌዎችን በማሰባሰብ፣ በየአካባቢው የተከሰቱ ግጭቶችና ጥቃቶችን ከእነ መንስዔዎቻቸውና መፍትሔያቸው ለመለየትና ለማጥናት መሞከሩ ነው የተነገረው፡፡

በውጤቱ ማወቅ የተቻለው ግን ሥር የሰደደ ችግር በሕዝብ መካከል አለመኖሩን ነው፡፡ የአገር ሽማግሌዎች ዕድሉ ከተሰጣቸውና የሚሉትን መስማት ከተቻለ የተፈጠሩትን ችግሮች ከማርገብ ባለፈ በዘላቂነት መፍታት የሚችሉ መሆናቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

በመሆኑም ግጭቱ፣ ጥቃቱና ጦርነቱ ባለባቸው አካባቢዎች የሃይማኖት አባቶች ከሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች ከአገር ሽማግሌዎች፣ እናቶች ከእናቶች፣ እህቶች ከእህቶች፣ ወጣቶች ከወጣቶችና፣ ምሁራን ከምሁራን ጋር በስፋት ውይይት እንዲያደርጉ ኮሚሽኑ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

በጦርነቱና ግጭቱ ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸውንና ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚችለውን በማድረግ መልሶ እንዲያቋቁሙ እንዲያደርግ የጠየቀው ኮሚሽኑ፣ አክቲቪስቶችም ሆኑ ጋዜጠኞች የሚያስተላልፏቸው መረጃዎች ግጭቶችን የሚያባብሱ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ እንዲያደርጉም አሳስቧል፡፡

የውጭ መንግሥታታ፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም ሆኑ ለትርፍ ያልተቋቋሙ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ግጭቶችን ለማስቆም የሚያደርጉት እንቅስቃሴ፣ የአገር ሉዓላዊነትን ከሚጥስና ከወገንተኝነት የፀዳ እንዲሆንም አሳስቧል፡፡ መጪው 2014 ሁሉም ነገር ተወግዶ የሰላም ዓመት እንዲሆን ምኞቱን ገልጿል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img