አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ነሐሴ 26፣ 2013 ― የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት አስተዳዳሪዋ ሳማንታ ፓወር ከሰሞኑ በአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ተደርገው የተሾሙት የቀድሞውን የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆን አግኝተው በኢትዮጵያ ጉዳይ መምከራቸውን አሳውቀዋል፡፡
ሳማንታ ፓወር ከኦባሳንጆ ጋር በተነበራቸው ቆይታ በቀጠለው የትግራይ ክልል ጦርነት የሰብአዊ አቅርቦት ለሚያስፈልጋቸው እንዲደርስ ማድረግ አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑ ላይ ከመግባባት ላይ ደርሰናል ብለዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ሆነው የተሰየሙት ኦባሳንጆ፣ በቀጠናው የሚገኙ ዋነኛ ተዋናዮችና የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር እንደሚሠሩ የተነገረላቸው ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ጉዳይ በተለይ ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ እንደሚሆንም ተጠብቆ ነበር፡፡