Friday, November 22, 2024
spot_img

ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር የሚያስችል ረቂቅ መመርያ አዘጋጀ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ነሐሴ 25፣ 2013 ― የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንክ ደንበኞችን መረጃ አያያዝ በተመለከተ አንድ ወጥ የሆነ አሠራር እንዲኖር አዲስ መመርያ ለማውጣት እየተዘጋጀ መሆኑ ተሰምቷል፡፡ በዚህ ዙሪያ የወጣው ረቂቅ ላይ ባንኮች እንዲመክሩበት እየተደረገ ይገኛል፡፡

መመርያ የሚወጣበትን ዓላማ በተመለከተ እንደተጠቀሰው፣ የአንድ ደንበኛ ማንነትን በትክክለኛው መንገድ ለማወቅና የገንዘብ እንቅስቃሴው ሕጋዊ መሆኑን ለማረጋገጥ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርንና ሽብርተኝነትን ከመከላከል አንፃር እንዲህ ያለውን አሠራር መዘርጋት አስፈላጊ በመሆኑ ጭምር ነው ተብሏል፡፡

መመርያው ከገንዘብ አስቀማጭ ደንበኞች መረጃ አያያዝ ጋር ተያይዞ ሊተገበሩ የሚገባቸውን አሠራሮች ያካተተ ሲሆን፣ ባንኮች ይህ መመርያ ከወጣ በኋላ ከአንድ ደንበኛ መጠየቅ የሚገባቸውን መረጃዎች በረቂቁ መመርያው ላይ በተመለከተው አሠራር መሠረት ተፈጻሚ እንዲያደርጉ ለባንኮች ኃላፊነት ተሰጥቷል፡፡

በረቂቅ መመርያው አጠራጣሪ እንቅስቃሴዎችን አያያዝና አስተዳደርን አስመልክቶ በአንቀጽ 8 በሠፈረው ድንጋጌ አጠራጣሪና ለሕገ ወጥ ዓላማ የተደረገ የገንዘብ ማስተላለፍ ድርጊት መለየትና መቆጣጠርንም ለባንኮች ኃላፊነት የሰጠ ሲሆን፣ ባንኮችም ሥራቸውን አፅንኦት ሰጥተው ኃላፊነት በተሞላበት፣ መልኩ በጥንቃቄ ማከናወን እንዳለባቸው ተጠቅሷል፡፡ ይህም በመመርያው የተቀመጠውን ገንዘብ የማውጣትና የማስተላለፍ ገደብ አለመጣሱን ማረጋገጥን ይጨምራል፡፡

አጠራጣሪ የገንዘብ ማስተላለፉ እንቅስቃሴን የመቆጣጠርና የመለየት ሒደትና ድርጊቱ መፈጸሙን የሚያሳይ በቂ ምክንያት ሲኖርና ወደ ድምዳሜ ሊያደርስ የሚያስችል በባንኮች በዝርዝር፣ አፅንኦትና በጥንቃቄ መታየትና ማገናዘብ ያለባቸውን ነገሮች አስቀምጧል፡፡

በመመርያ በተጠቀሰው መሠረት ባንኮች አጠራጣሪ የገንዘብ ማስተላለፍ ውስጥ ተሳትፏል ያሉትን ደንበኛ የሥራ ግንኙነት በአፋጣኝ ማቋረጥ አለባቸው፡፡ በተጨማሪም የደንበኛውን ዝርዝር ግለ ታሪክና ተዛማጅ ማስረጃዎችን የባንክ ደብተሩ ቅጂ፣ የፊርማ ናሙና፣ መታወቂያና የገንዘብ ዝውውር ሪፖርት ለተጨማሪ ምርመራና አስፈላጊውን ሕጋዊ ርምጃ ለመውሰድ እንዲረዳ ለፋይናንስ ደኅንነት ማዕከል መላክ ይኖርባቸዋል፡፡ መረጃውን ለሌሎች ባንኮች ለማሠራጨት ተገቢውን ጥንቃቄና በእነሱ በኩል ለሚያደርጉት ተመሳሳይ ምልከታ እንዲረዳም ለብሔራዊ ባንክ መላክ አለበት፡፡

መመርያው ተያያዥ የገንዘብ እንቅስቃሴዎችን የተመለከቱ አንቀጾችንም ያካተተ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ባንኮች በደብዳቤ እንዲፈጽሟቸው የተላለፈን አሠራር በመመርያ ደረጃ እንዲወጣ ተብሎ የተካተተ ስለመሆኑም ለማወቅ ተችሏል፡፡ እንዲህ ባለው መንገድ በመመርያው እንዲካተቱ ከተደረጉት ውስጥ ከዚህ ቀደም አንደ ደንበኛ በሳምንት ውስጥ ማንቀሳቀስ የሚችለው አምስት ጊዜ ብቻ መሆኑን የሚጠቁመው ይገኝበታል፡፡ አሁንም ባንኮች ይህን አሠራር የሚጠቀሙበት ሲሆን፣ ራሱን በቻለ መመርያ ባለመውጣቱ በመመርያው ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል፡፡

ባንኮች በረቂቁ ላይ ያላቸውን ሐሳብ እየሰጡ ሲሆን፣ ተጨማሪ ግብዓቶች ታክለውበትና ፀድቆ መመርያው በቅርቡ ሥራ ላይ ይውላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በኢትዮጵያ በሚገኙ ባንኮች የቁጠባ ደብተር የከፈቱ ዜጎች ቁጥር ከ66 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ መድረሳቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img