Friday, November 22, 2024
spot_img

ዕርዳታ ለማድረስ ወደ ትግራይ ክልል የተላኩ 72 የጭነት ተሽከርካሪዎች እንዳልተመለሱ ተነገረ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ነሐሴ 24፣ 2013 ― በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከተከሰተው ጦርነት ጋር በተያያዘ በትግራይ ክልል የዕለት ደራሽ ዕርዳታ ለሚያስፈልቸው ዜጎች ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ሰብዓዊ ዕርዳታ ጭነት ይዘው ወደ ትግራይ ክልል የተላኩ 72 የጭነት ተሽከርካሪዎች፣ ጭነታቸውን አራግፈው አለመመለሳቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡

በፌዴራል መንግሥትና በዕርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች አማካይነት በተዘጋጀው መመርያ መሠረት፣ ዕርዳታ ወደ ትግራይ ክልል ይዘው የሚሄዱ ተሽከርካሪዎች ጭነታቸውን አድርሰው እንዲመለሱ የሚፈቀደው ከሦስት አስከ አምስት ቀናት ብቻ ቢሆንም፣ የተላኩት ተሽከርካሪዎች ከሐምሌ 14፣ 2013 ጀምሮ ለአንድ ወር ያህል አለመመለሳቸው ተገልጿል፡፡

ይህንኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታርያት ኃላፊ ቢልለኔ ሥዩም ለውጭ ጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ተሽከርካሪዎቹ ባለመመለሳቸው እንቅፋት በመፈጠሩ ተጠያቂ ሊኖር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

አያይዘውም ዕርዳታ ድርጅቶች አማካይነት ሲቀርብ የነበረውን እህል ለጫኑ ተሽከርካሪዎች የፍተሻ ጣቢያዎች ብዛት በማስተካከል፣ በፊት ከነበሩት ሰባት ጣቢያዎች በቴክኖሎጂ በመታገዝ ወደ ሦስት ዝቅ እንዲሉ መደረጉን አክለው ገልጸዋል፡፡

ከዘጠኝ ወራት በላይ ባስቆጠረው በሕወሃት ታጣቂዎችና በአገር መከላከያ ሠራዊት መካከል በሚካሄደው ጦርነት፣ በትግራይ ክልል ከ5 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የሰብዓዊ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገልጿል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img