Sunday, October 6, 2024
spot_img

ኦነግ የነ አራርሶ ቢቂላ ቡድን ከብልጽግና ጋር በመቀናጀት ፓርቲውን ለማፍረስ እየሠራ ነው ሲል ከሰሰ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ነሐሴ 22፣ 2013 ― በኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ በተነበበ መግለጫ አራርሶ ቢቂላ፣ ኢብሳ ነገዎ፣ ቶሌራ አዳባ፣ ቀጄላ መርዳሳ እና አቶምሳ ኩምሳ ከብልፅግና ጋር በመቀናጀት ፓርቲውን ለማፍረስ እና ህዝቡን ለማደናገር እየሰሩ እንደሚገኙ ሠፍሯል፡፡

ግለሰቦቹ የሚመሩት ቡድን ‹‹በኦሮሞ ህዝብ እና ብሄር ብሄረሰቦች ዘንድ የሂልተኑ ኦነግ ወይም የብልጽግና ኦነግ በሚል ስያሜ›› እንደሚታወቁ የገለጸው መግለጫው፣ ተገንጥለውዋል ያላቸው ግለሰቦች ‹‹የኦነግ ከፍተኛ አመራሮችን አሳስረው የፓርቲውን ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳን በቁም እስር አስቀምጠው ራሳቸውን በራሳቸው ሊቀመንበር እና ምክትል ሊቀመንበር አድርገው ከሾሙ በኋላ ፓርቲውን የማጥፋት ተግባራቸውን ተያይዘውታል›› ሲልም ወንጅሏል፡፡

መግለጫው አባላቶቹን በአሁኑ ወቅት ገዢው ብልጽግና ‹‹በሁሉም አቅጣጫ›› በውጥረት ውስጥ ገብቶበታል በማለትም በኦነግ ፓርቲ ስም አስመስለው መግለጫ በማውጣት በመንግሥት ሚዲያ እና ከመንግሥት ካድሬዎች ጋር በጋራ በመሆን ‹‹ራሳቸውን ልክ የፓርቲው አመራር በማስመሰል እየነገዱ›› ይገኛሉ ያለ ሲሆን፣ ‹‹በመላው ኦሮሞ ህዝብ ላይም በተለየ መልኩ ዘመቻ ከፍተዋል›› ብሏል፡፡

እነ አራርሶ ቢቂላ ብልጽግና ላይ ተደቅኗል ያለውን ውጥረት ለማርገብም በሚያደርጉት ተግባር ውስጥ እነርሱን ጨምሮ ላለፉት 21 ዓመታት በላይ ‹‹ኦነግን የማያውቁት እና ምንም ተሳትፎ ያልነበራቸው አካላት›› ያላቸው ገላሳ ዲልቦ እና ዲማ ነገዎ የመሳሰሉ ግለሰቦችን ‹‹ከብልፅግና ጋር በመጣመር በኦሮሞ ህዝብ ላይ ዘመቻ›› እንደከፈቱ በመግለጽ፣ ‹‹የኦሮሞ ህዝብም ይህንን አፍራሽ ድርጊታቸውን በመረዳት ራሱን ከእንደነዚህ አይነት ግለሰቦች እንዲጠብቅ›› ሲል አሳስቧል፡፡

መግለጫው እንደ አራርሶ ቢቂላ፣ ቀጄላ መርዳሳ እና እነሱን የመሳሰሉ አካላት የፓርቲው ሊቀመንበር እና ምክትል ሊቀመንበር ደረጃ ‹‹ለራሳቸው በመስጠት በተለያዩ የብልጽግና መድረኮች ላይ በመገኘት›› እየፈጠሩት ነው ያለውን ‹‹ማደናገር›› ኦነግን የሚወክል አይደለም ብሏል፡፡

በኢትዮጵያ ከሦስት ዓመታት በፊት የተፈጠረውን የፖለቲካ ለውጥ ተከትሎ ወደ አገር ቤት የተመለሰው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር፣ ባለፉት ጊዜያት ሊቀመንበሩ ዳውድ ኢብሳ በአንድ ወገን፣ ምክትሉ አራርሶ ቢቂላ በሌላ ወገን በሚያወጧቸው የተለያዩ መግለጫዎች አንዱ ለሌላው እውቅና ሲነፍግ መሰንበቱ ይታወቃል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img