Thursday, November 21, 2024
spot_img

የባይደን አስተዳደር ኢትዮጵያ ከአጎዋ ልትሰረዝ እንደምትችል በይፋ ማሳወቁ ተሰማ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ነሐሴ 20፣ 2013 ― ኢትዮጵያ በአሜሪካ መንግሥት ከ20 ዓመታት በፊት የተሰጣትን ከታሪፍና ከኮታ ነፃ የሚያደርገውን ‹‹አፍሪካን ግሮውዝ ኤንድ ኦፖርቹኒቲ አክት›› (አጎዋ) ተጠቃሚነት ልታጣ እንደምትችል የባይደን አስተዳደር በይፋ ማሳወቁ ተሰምቷል፡፡

ይህንኑ ለሕወሓት በሎቢ አድራጊነት የሚሠራውና ኢትዮጵያን ከአጎዋ ለማሰረዝ እየሠራ መሆኑን የሚናገረው ቮን ባተንግ ሞንግዩ በትዊተር ገጹ አስታውቋል፡፡ እንደ ቡድኑ ከሆነ አሜሪካ የኢትዮጵያ የአጎዋ እድል አደጋ እንዳንዣበበት ያሳወቀችው በትግራይ ክልል ተፈጽመዋል ከተባሉ ሁኔታዎች ጋር ነው፡፡

የመንግሥት ተቃዋሚ የሆነው ይህ ቡድን ኢትዮጵያን ከ20 ዓመታት በላይ ተጠቃሚ የሆነችበት የአጎዋ ዕድል እንዳይቀጥል ከአንድ ወር በፊት ጀምሮ እንቅስቃሴ መጀመሩ መነገሩ የሚታወስ ነው፡፡ ቡድኑ የአቤቱታ ደብዳቤውን ለአሜሪካ መንግሥትና ለኮንግረስ ማስገባቱም ተሰምቶ ነበር፡፡

በአንጻሩ የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት ለማሰረዝ የሚንቀሳቀሰውን ቡድን ሐሳብ ለማክሸፍ ደግሞ ‹‹አሜሪካን ኢትዮጵያን ፐብሊክ አፌይርስ ኮሚቴ›› የተሰኘ ሌላ ቡድን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚ ኃይል ኢትዮጵያ ከዕቅዱ ተጠቃሚነት እንድትሰረዝ ያቀረበውን ጥያቄ የአሜሪካ መንግሥት ውድቅ እንዲያደርግ ግፊት እያደረገ መሆኑ ታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ ከአጎዋ ተጠቃሚነት እንድትሰረዝ በአሜሪካ አገር ያሉ የሕወሓት ደጋፊዎች አጎዋን የፖለቲካ መጠቀሚያ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን፣ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስቀድመው ቡድን ባወጣው ሰነድ አስታውቆ ነበር፡፡

አጎዋ በአሁኑ ጊዜ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ቀጥረው የሚያሠሩ የውጭ አገር ባለሐብቶችና አልሚዎች፣ ወደ ኢትዮጵያ የመጡበት ትልቁ ምክንያታቸው መሆኑን ባለሞያዎች ይናገራሉ፡፡

ኢትዮጵያ በ2012 ብቻ በዚህ የነፃ ገበያ ዕድል ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚገመቱ ምርቶች ወደ አሜሪካ መላኳን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img