Tuesday, December 3, 2024
spot_img

ራሚስ ባንክ ለመመሥረት የሚያስችለውን የተከፈለ ካፒታል ማሰባሰብ መቻሉን አስታወቀ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ነሐሴ 19፣ 2013 ― ሙሉ በሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ባንክ ለማቋቋም በመንቀሳቀስ ላይ ከሚገኙት ባንኮች ውስጥ በምሥረታ ላይ የሚገኘው ራሚስ ባንክ፣ ባንኩን ለመመሥረት የሚያስችለውን የተከፈለ የ500 ሚሊዮን ብር ካፒታል ማሰባሰቡን ገልጧል፡፡

ሪፖርተር የባንኩን አደራጆች ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ራሚስ ባንክ በተፈቀደ ሁለት ቢሊዮን ብር ካፒታል ለመቋቋም ወደ አክሲዮን ሽያጭ የገባ ሲሆን፣ ባንክ ሲመሠረት የሚያስፈልገውን የ500 ሚሊዮን ብር ካፒታል ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ላይ ማሟላት በመቻሉ ወደ ባንክ ምሥረታው ሒደት ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ባንኩ የ500 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታሉን ማሟላቱን አስመልክቶ በቀጣይ ሁለት ሳምንታት ለብሔራዊ ባንክ አስታውቆ ምሥረታውን ዕውን ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ራሚስ ባንክ ባንኩን ለማቋቋም የሚጠበቅበትን የ500 ሚሊዮን ብር ካፒታል ማሟላቱን ከማረጋገጡ በፊት በተመሳሳይ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ ባንክ ለመመሥረት የአክሲዮን ሽያጩን ሲያካሂድ ከነበረው ዛድ ባንክ ጋር ለመዋሃድ የሚያስችለውን ስምምነት ለመፈራረም በዝግጅት ላይ ነበር፡፡

እንደ ራሚስ ባንክ አደራጆች ባንካቸው ራሱን ችሎ ባንክ ለማቋቋም የሚያስችለውን ካፒታል ቢያሟላም ከዛድ ባንክ ጋር ለመዋሃድ የተደረሰው ስምምነት የሚቀጥል ሲሆን፣ በቅርቡ የመግባቢያ ሰነድ ለመፈራረም በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡

ዛድ ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሰጥ ራሱን የቻለ ባንክ ለማቋቋም ወደ አክሲዮን ሽያጭ ውስጥ ከገቡት ስድስት ባንኮች መካከል አንዱ ሲሆን፣ እስካሁን ባካሄድ የአክሲዮን ሽያጭ ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል አሰባስቦ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አክሲዮን በመሸጥ ላይ የነበሩ ባንኮች በ500 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ባንክ መመሥረት እንዲችሉ የተሰጣቸው የጊዜ ገደብ በመጠናቀቅ ላይ በመሆኑ፣ ባንኮቹ በአክሲዮን ሽያጭ የሰበሰቡትን ካፒታል በማቀላቀል የሚፈለገውን የ500 ሚሊዮን ብር ካፒታል አሟልተው ወደ ሥራ ለመግባት ተስማምተው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ባንክ ለማቋቋም በምሥረታ ላይ ከቆዩት ባንኮች ውስጥ ወደ ሥራ የገባው ዘምዘም ባንክ ነው፡፡ ከወለድ ነፃ ባንክ ለማቋቋም የሚያስችለውን የተከፈለ ካፒታል በማሟላት ወደ ሥራ ለመግባት በዝግጅት ላይ ያለው ሌላው ባንክ ደግሞ ሒጅራ ባንክ መሆኑም ይታወቃል፡፡

ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት የሚሰጥ ባንክ ለማቋቋም የሚፈቅደው ሕግ ከመውጣቱ ቀደም ብሎ ባንኮች ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በመስኮት ደረጃ እንዲሰጡ በተፈቀደው መሠረት እስካሁን ወደ 11 ባንኮች አገልግሎቱን በመስጠት ላይ ናቸው፡፡

ይህ በመስኮት ደረጃ የሚሰጠው አገልግሎት ከተጀመረ ወዲህ እነዚህ ባንኮች ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ያሰባሰቡት የተቀማጭ ገንዘብ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ ከዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ ከወለድ ነፃ ያሰባሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን በ2013 ሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ ከ64 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱንም ዘገባው አመልክቷል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img