Saturday, November 23, 2024
spot_img

በምሥራቅ ወለጋ በተፈጸመ ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸው ተነገረ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ነሐሴ 19፣ 2013 ― በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪራሙ ወረዳ ከዛሬ ሳምንት ነሐሴ 12 ጀምሮ በታጣቂዎች ተፈጽሟል በተባለ ጥቃት እና ግጭት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን ከጥቃቱ የተረፉ ነዋሪዎች እና የዞኑ አስተዳዳሪ ነግረውኛል ሲል ቢቢሲ አስነብቧል፡፡

ጥቃቱ የደረሰው በስፍራው የነበረው የኦሮሚያ ልዩ ኃይል ከስፍራው መውጣቱን ተከትሎ መሆኑን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል ነው የተባለው፡፡

የምሥራቅ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አለማየሁ ተስፋ በበኩላቸው ከአምስት ቀናት በፊት በአካባቢው ግጭት እንደነበረ አረጋግጠው፤ ጉዳት የደረሰው ‹‹የጁንታው ተላላኪ በሆነው ሽፍታው ሸኔ እና በታጠቁ አማራዎች›› ምክንያት ነው ማለታቸው ተመላክቷል፡፡

ጨምረውም ‹‹ጥቃቱን በዋናነት የሸኔ ሽፍታዎችና የጁንታው ተላላኪዎች ናቸው በኦሮሞና በአማራ ሕዝብ ላይ ተኩስ በመክፈት የፈጸሙት። ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ የአማራ ታጣቂዎችም አሉ። አሁን ግጭቱ ቆሟል›› ብለዋል።

አቶ አለማሁ ‹‹በአሁኑ ወቅት የፀጥታ አካላት ገብተው እርምጃ እየወሰዱና ሕዝቡን እያረጋጉ ነው። እስካሁን ድረስ በግጭቱ የሞተውና የተጎዳው ሰው ቁጥር እየተጣራ ነው። ውጤቱ ሲደርስ እናሳውቃለን›› ሲሉም ተናግረዋል።

አስተዳዳሪው በስፍራው ይንቀሳቀሳሉ ያሏቸው ‹‹ሽፍታው ሸኔ እና የአማራ ታጣቂዎች›› የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸውን ተናግረው፤ ‹‹እነዚህ ሁለት ቡድኖች እርስ በእርሳቸው ተታኩሰዋል። ሕዝብም ላይ ተኩሰዋል›› ብለዋል።

የሁለቱ ቡድን ዓላማ ‹‹ለብዙ ዓመታት አብሮ በሰላም የኖረን ብሔር ማጋጨት ነው›› ያሉት አቶ አለማየሁ፤ በግጭቱ የሰዎች ሕይወት ማለፉን እና በርካታ ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን አረጋግጠዋል።

በጥቃቱ የተጎዱ ሰዎችን ቁጥር በተመለከተ ከተለያዩ ወገኖች መጠኑ የተለያየ አሃዝ መገኘቱን እንዲሁም በንብረትም በኩል ቤቶች መቃጠላቸውንና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ከጥቃቱ ሽሽት ቤት ንብረታቸውን ትተው ወደ አቅራቢያ አካባቢዎች መሄዳቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡

መንግሥት ሸኔ የሚለውና በሽብርተኛነት የተፈረጀው እንዲሁም በቅርቡ ከሌላኛው በሽብር የተፈረጀው ሕወሓት ጋር ጥምረት መፍጠሩን ያሳወቀው ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር፣ አሁን ጥቃቱ በተፈጸመበት አካባቢ ታጣቂዎቹ ከዚህ በፊት ጥቃት መፈጸማቸው መነገሩ አይዘነጋም።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img