Monday, September 23, 2024
spot_img

አሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት የኤርትራ ጦር ዳግም ወደ ትግራይ እየተሰማራ ነው አሉ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ነሐሴ 19፣ 2013 ― አሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረት የኤርትራ ጦር በቅርብ ቀናት ውስጥ ዳግም ወደ ትግራይ እየገባ መሆኑን በመጥቀስ፣ ጉዳዩ እንዳሳሰባቸው እየገለጹ መሆኑን የሚጠቁሙ መረጃዎች ወጥተዋል፡፡

የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ከትላንት በስቲያ ሰኞ ነሐሴ 17 ‹‹የኤርትራ ጦር ሰኔ ወር ላይ ከወጣ በኋላ በበርካታ ቁጥር ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ተመለሶ ገብቷል›› ማለታቸውን ሬውተርስ የዜና ወኪል በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡

የአውሮፓ ኅብረት ዲፕሎማቶች ደግሞ ነሐሴ 14 ጽፈውታል በተባለ የውስጥ ማስታወሻ ኤርትራ የትግራይ ድንበርን ተሻግረው የገቡ ተጨማሪ ኃይሎች አሰማርታለች ማለቱም ተመላክቷል፡፡

ይህ የአንቶኒ ብሊንከን እና የአውሮፓ ኅብረት ማሳሰቢያ የተሰማው አሜሪካ በትግራይ ክልል ከተካሄደው ጦርነት ጋር በተያያዘ የኤርትራ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ላይ በሰብአዊ መብቶች ጥሰት ምክንያት ማዕቀብ መጣሏን ካስታወቀች በኋላ ነው።

ጄነራል ፊሊጶስ ወልደዮሐንስ፤ በጦርነቱ ውስጥ በከባድ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የሚከሰሰው የኤርትራ ሠራዊት መሪ ወይም ከፍተኛ ባለሥልጣን በመሆናቸው ማዕቀቡ ተጥሎባቸዋል።

የአውሮፓ ኅብረት የውስጥ ማስታወሻ የተባለ ሰነድ ኤርትራ የይገባኛል ጥያቄ በሚነሱባቸው ምዕራብ ትግራይ አካባቢዎች ጦሯን አስፍራለች ይላል።

እንደ ሬውተርስ የዜና ወኪል ከሆነ የአውሮፓ ኅብረት የውስጥ ማስታወሻ፣ የኤርትራ ጦር አዲ ጎሹ እና ሑመራ ከተሞች አካባቢ ‹‹ታንክ እና ከባድ መሣሪያዎችን በመታጠቅ መከላከያ ቦታ ይዟል›› ይላል።

ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ቱርክ ከማቅናታቸው ከአንድ ቀን በፊት ማለትም ነሐሴ 11 ወደ አስመራ ተጉዘው ነበር ያለ ሲሆን፣ ማስታወሻው ጠቅላይ ሚንስትሩ ወደ አስመራ ስለማቅናታቸው ይፋ አለመደረጉን አስታውሷል።

የዜና ወኪሉ በጉዳዩ ላይ ከኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴርም ሆነ ከኢትዮጵያ በኩል ምለሽ አላገኘሁም ነው ያለው፡፡

ዘጠኝ ወራት ባስቆጠረው በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተውበታል በሚባለው የትግራይ ጦርነት የኤርትራ ጦር ከፌደራል መንግሥት ጎን ተሰልፎ መዋጋቱ ይታወቃል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img