Sunday, September 22, 2024
spot_img

ብሔራዊ ባንክ ዕግድ ስለጣለባቸው ንብረቶች ባለሥልጣኑ ማብራሪያ ጠየቀ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ነሐሴ 17፣ 2013 ― በቅርቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ንብረቶችን በዋስትና በማስያዝ የሚሰጥ ብድር በማገዱ ምክንያት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአሽከርካሪዎችና ተሽከርካሪዎች ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ማብራሪያ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡

ሕንፃዎች፣ ቤቶች፣ መሬትና ሌሎች ንብረቶችን በዋስትና በማስያዝ የሚሰጥ ብድርን በሚመለከት የወጣው ዕገዳ ተሽከርካሪዎችን ማካተቱንና አለማካተቱን መመርያው ስለማይገልጽ፣ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጡ መጠየቁን የባለሥልጣኑ የተሽከርካሪዎች ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ዘለቀ ተናግረዋል፡፡

ሕንፃዎችን፣ ቤቶችን፣ መሬትና ሌሎች ንብረቶች መያዣ በማድረግ የሚሰጥ ብድር እንዳይሰጥ ቢታዘዝም፣ ዕግዱ ተሽከርካሪን ያካተተ መሆን አለመሆኑን እስኪረጋገጥ ድረስ በባለሥልጣኑ የሚሰጠው አገልግሎት ከነሐሴ 10፣ 2013 ጀምሮ ተቋርጧል፡፡

ከተለያዩ ባንኮች ተበድረው በባለሥልጣኑ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ተሽከርካሪዎች እንዳይሸጡ እንዳይለወጡ ለማሳገድ ለሚቀርቡ ተገልጋዮች፣ አገልግሎት ለጊዜው መቋረጡን አቶ ዳዊት ገልጸዋል፡፡

አገልግሎቱ የተቋረጠው ብሔራዊ ባንክ ያወጣው መመርያ ተሽከርካሪዎችን ያካተትታል ወይ አያካትትም የሚለው ማብራሪያ ለባለሥልጣኑ እስኪነገረው መሆኑ ተገልጿል፡፡ ባንኮች ለሰጧቸው ብድሮች ማስያዣ የተሽከርካሪዎች ሊብሬዎች እነሱ ዘንድ ቢኖሩም፣ ተሽከርካሪዎቹ እንዳይሸጡ እንዳይለወጡ ማገድ የባለሥልጣኑ ኃላፊነት በመሆኑ በጊዜያዊነት አገልግሎት ማቋረጣቸውን አቶ ዳዊት አብራርተዋል፡፡

አቶ ዳዊት እንዳስረዱት ሕንፃ፣ ቤት፣ መሬትና ሌሎች ንብረቶች ለብድር ማስያዣነት እንዳይውሉ መታገዳቸውን መመርያው ቢገልጽም፣ ስለተሽከርካሪዎች መታገድ አይታወቅም፡፡

ነገር ግን በመመርያው ላይ ‹‹ሌሎችም›› የሚለው ማናቸውም ለብድር መያዣነት የሚውሉ ንብረቶች ክልክል ናቸው›› በሚል በመረዳታቸው፣ ተሽከርካሪዎችን ማገዳቸውን አቶ ዳዊት አብራርተዋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ለባንኮች በላከው መመርያ ንብረቶችን ለብድር መያዣነት መጠቀም መከልከሉን እንደተረዱ የተናገሩት አቶ ዳዊት፣ ይህንን በይበልጥ ለማጥራትና ተገልጋዮች እንዳይንገላቱ ለብሔራዊ ባንክ ደብዳቤ መጻፋቸውን መግለጻቸውን ሪፖርተር ዘግቧል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ነሐሴ 6፣ 2013 ባንኮች ቤት፣ ሕንፃ፣ መሬትና ሌሎችም ንብረቶችን በመያዣነት ተጠቅመው ብድር እንዳይሰጡ ማገዱ ይታወሳል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img