Sunday, October 6, 2024
spot_img

የሱማሌ ክልል ከአፋር ጋር ያለው የድንበር ውዝግብ የተባባሰ ችግር እንዳይፈጥር ስጋት ገብቶኛል አለ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ነሐሴ 17፣ 2013 ― በአፋር እና በሱማሌ ክልል መካከል ያለው የድንበር ውዝግብ የተባባሰ ችግር እንዳይፈጠር ስጋት መሆኑን የሱማሌ ክልል መንግሥት አስታውቋል፡፡

በሁለቱ ክልሎች መካከል ውዝግብ ከተፈጠረበት ድንበር አከባቢ የተፈናቀሉት የሱማሌ ክልል ማኅበረሰቦች እስካሁን ወደየመኖሪያ ቦታቸው አለመመለሳቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ተፈናቃዮች ወደ ቦታቸው መመለስ ያልቻሉት ችግሩ መፍትሔ ባለማግኘቱ ነው ተብሏል።

የሱማሌ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ዳይሬክተር መሐመድ ሮብሌ ‹‹አፋሮች ቦታውን አንለቅላችሁም በማለታቸውና ተፈናቃዮቹ ቦታችንን በኃይል እንመልሳለን የሚል አስተሳሰብን ስለሚያንጸባርቁ ብጥብጥ ይነሳል የሚል ስጋት ፈጥሯል›› ሲሉ እንደነገሩት አዲስ ማለዳ ጋዜጣ አስነብቧል፡፡

ዳይሬክተሩ እንዳሉት፣ ከአሁን በፊት በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ሰዎች ለሕልፈተ ሕይወት እንደተዳረጉና በዚህም ክስተት ሴቶችና ሕጻናትን ጨምሮ በርካቶች የችግሩን ገፈት የቀመሱ ሲሆን፣ ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው በተለያዩ መጠለያዎች ተጠግተው የሚገኙ የሱማሌ ማኅበረሶቦችም ከ30 ሺሕ በላይ ናቸው።

የሱማሌ ክልል መንግሥት እና ማኅበረሰቡ ችግሩን ለመቅረፍ የተፈናቀሉትን ለማግባባት እየሞከሩ ቢሆንም፣ በክልሎቹ መካከል ብጥብጥ ያስነሱ ድንበሮችን በተመለከተ ምንም አይነት መፍትሔ ላይ አልተደረሰም ተብሏል። ‹‹ክረምቱን በስደት መቋቋም አልቻልንም ሲሉ የሚሰሙት ማኅበረሰቦች ትዕግስታቸው ያለቀ ይመስላልና ለዳግም ብጥብጥ እንዳይነሳሱ የሚል ስጋት ተፈጥሯል›› ሲሉ ዳይሬክተሩ አክለዋል።

ጋዜጣው በጉዳዩ ላይ የአፋር ክልል መንግሥትን አስተያየት ለማግኘት በተደጋጋሚ ስልክ ብመታም ጥረቴ አላተሳካም ብሏል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img