አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ነሐሴ 17፣ 2013 ― በጸጥታ ችግር ምክንያት ከትግራይ ክልል ተፈናቅለው አዲስ አበባ የሚገኙ የመቐለ፣ አክሱም፣ የዓዲግራት እና ራያ ዩኒቨርስቲ መምህራን ከኹለት እስከ ሦስት ወር ደሞዝ ባለመከፈላቸው ችግር ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በአራቱ ዩኒቨርስቲዎች ሲያስተምሩ የነበሩት መምህራን እንደገለጹት የደሞዝ ክፍያው የተዛባው ከጥቅምት 2013 ጀምሮ ቢሆንም፣ በመሀል በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ተወካዮች በኩል ክፍያ ተፈጽሞ ነበር ብለዋል።
እንደ ቅሬታ አቅራቢ መምህራን ከግንቦት ወር ጀምሮ እስካሁን ድረስ በአንዳንድ ዩኒቨርስቲዎች የሦስት ወር ደሞዝ እንዳልተከፈላቸውና ባንክ ላይ ያላቸውን ገንዘብ አውጥተው እንዳይጠቀሙ የባንክ አካውንታቸው መታገዱን መግለጻቸውን የአዲስ መለዳ ጋዜጣ ዘገባ ያመለክታል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም መምህራኑ የሚሠሩባቸው ዩኒቨርስቲዎች በሚገኙበት አካባቢ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ዝውውር ቢጠይቁም ጥያቄያቸው ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱን ተናግረዋል።
የተለያዩ መምህራን ተደራጅተው ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት የደሞዝ ጥያቄ በደብዳቤ ያቀረቡ ሲሆን፣ ሚኒስቴሩም ጉዳያቸውን ለማስፈጸም ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከብሔራዊ ባንክ እና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር እየሠራ እንደሚገኝ ገልጾላቸው ነበር።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይህንን ቢገልጽም፣ ይህ ዜና እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ደሞዛቸው እንዳልተከፈላቸውና የአብዛኞቹ መምህራን የባንክ አካውንት እንዳልተለቀቀላቸው ነው ቅሬታ አቅራቢዎቹ የገለጹት።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ መምህራን መንግሥት በአፋጣኝ እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል።