Sunday, September 22, 2024
spot_img

የዓለማችን የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ የዘረ መል ክትባት ፈቃድ አገኘ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ነሐሴ 15፣ 2013 ― ኮሮና ቫይረስን መከላከል ያስችላል የተባለው የዓለማችን የመጀመሪያው የዘረመል ክትባት ለአስቸኳይ ጊዜ ጥቅም ላይ እንዲውል የሕንድ መድኃኒቶች ተቆጣጣሪ ተቋም ፈቃድ ሰጥቷል፡፡

በሦስት ዙር የሚሰጠው ዚኮቭ-ዲ የሚባለው ይህ የዘረ መል ክትባት ሙከራ በተደረገባቸው ሰዎች ላይ ምልክት የሚያሳየውን የወረርሽኙን መስፋፋት በ66 በመቶ መከላከል መቻሉን ክትባቱን ያዘጋጀው ካዲላ ሔልዝኬር የተባለው ድርጅት ያዘጋጀው ጥናት አመልክቷል።

ይህን በሕንድ ውስጥ ሲዘጋጅ ሁለተኛ የሆነው የኮሮናቫይረስ ክትባት በዓመት 120 ሚሊዮን ብልቃጦችን ለማምረት ዕቅድ እንዳለው የመድኃኒት አምራቹ አሳውቋል።

ከዚህ በፊት የተሰሩ የዘረመል ክትባቶች በእንስሳት ላይ ውጤታማ የሆኑ ሲሆን፣ በሰው ላይ ግን ሊሳኩ አልቻሉም ነበር።

ይህን አዲሱን የዘረ መል ክትባት ያዘጋጀው ካዲላ ሔልዝ ኬር እንደሚለው በሕንድ ውስጥ በሚገኙ ከ50 በላይ ማዕከላት ውስጥ 28 ሺህ ፈቃደኞች የተሳተፉበት ትልቁን ክሊኒካዊ ሙከራ አድርጓል።

በተጨማሪም ክትባቱ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ሺህ በሚሆኑ እድሜያቸው ከ12 አስከ 18 በሆኑ ታዳጊዎች ላይ ሙከራ ተደርጓል። በዚህም ክትባቱ ለታዳጊዎች ‹‹ተስማሚና ደኅንነቱ የተጠበቀ” ሆኖ እንዳገኘው ገልጿል።

ዋነኛው የክትባቱ ሦስተኛ ዙር ሙከራ ሕንድ በወረርሽኙ ክፉኛ ተመትታ በነበረበት ጊዜ በመሆኑ ዴልታ የተባለውን የመሳሰሉ “አደገኛ ልውጥ የኮቪድ ዝርያዎችንም ሊከላከል እንደሚችል” እምነት እንዳለ ተገልጿል።

የሕይወት መዋቅር ከሆኑት መካከል አንዱ የሆነው ዘረመል (ዲኤንኤ) አንድ ሰው ከቤተሰቡ የሚተላለፍ የዘር መረጃን የሚይዝ ነው።

እንደ ሌሎቹ ክትባቶች ሁሉ የዘረመል ክትባት አንድ ጊዜ ከተወሰደ የሰውነታችን በሽታን የመከላከል ተፈጥሯዊ ሥርዓት ቫይረሱን እንዲከላከል ያደርገዋል።

ይህ አሁን በሕንድ ጥቅም ላይ እንዲውል የተፈቀደው የዘረ መል ክትባት የዓለማችን የመጀመሪያው ለሰው ልጅ የተዘጋጀ የኮቪድ-19 ክትባት ነው።

የፈረሶችን በሽታና በውሾች ላይ የሚከሰት የቆዳ ካንስርን ለመከላከል የሚያስችሉትን ጨምሮ በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ ውስጥ ለእንስሳት የሚሰጡ በርካታ የዘረመል ክትባቶች ይገኛሉ።

ተመራማሪዎች እንደሚሉት የዘረመል ክትባቶች ከሌላ አይነት ክትባቶች አንጻር ርካሽ፣ ደኅንነታቸው የተጠበቀና አስተማማኝ ከመሆናቸው በተጨማሪ ለረጅም ጊዜ ለማቆየትና ለማጓጓዝ ምቹ ናቸው።

ከዚህ በፊት በሰው ላይ የሚከሰቱ በሽታዎችን ለመከላከል የተዘጋጁ የዘረመል ክትባቶች በተለያዩ ምክንያቶች ሳቢያ ውጤት ሳያስገኙ ቆይተዋል።

አሁን ተዘጋጀ የተባለው የኮሮናቫይረስ መከላከያ የዘረመል ክትባት ከዚህ በፊት ከተገኙት የወረርሽኙ ክትባቶች የሚለየው በሦስት ዙር የሚሰጥ መሆኑ ሲሆን አምራቹ በሁለት ዙር ለመስጠት የሚቻልበትን ሁኔታ እያጠና እንደሚገኝ አመልክቷል መባሉን የዘገበው ቢቢሲ ነው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img