አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ነሐሴ 15፣ 2013 ― በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ሕወሃት በቀጣናው ካሉ የሽብር ቡድኖች ጋር እደረገው ነው ያለው ‹‹መጥፎ›› ትብብር አጋሮች በጥንቃቄ እንዲመለከቱት የኢትዮጵያ መንግስት ጠይቋል፡፡
ይህንኑ የመንግስት አቋም ያንጸባረቁት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬተሪያት ቢልለኔ ሥዩም፣ ትላንት በሰጡት መግለጫ ሕወሓት አሁንም የሽብር ድርጊት እየፈጸመ ይገኛል ያሉ ሲሆን፣ ቡድኑ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ቀንድ የሰላም እና ጸጥታ ችግር እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡
ሁሉም ዓለም አቀፍ አጋሮች፤ ሕወሃት በአፍሪካ ቀንድ ካሉ ዓለም አቀፍ የሽብር ቡድኖች ጋር ያለውን መጥፎ ትብብር በጥንቃቄ ሊመለከቱት እንደሚገባ የገለጹት ቢልለኔ፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ሕወሃት የሚፈጽማቸውን ‹‹የሽብር›› ሲሉ የጠሯቸውን ድርጊቶች ሊያወግዝ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ሕወሃት በቅርቡ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ጥቃት መፈጸሙን እና ሰርጎ በገባባቸው አካባቢዎች በከፍተኛ ደረጃ ሕዝብ ማሸበሩን፤ የግለሰቦችን ንብረት መዝረፉን፤ የሕክምና ተቋማትን ጨምሮ የመሰረተ ልማት አውታሮችን እያወደመ መቀጠሉን ቢለኔ ተናግረዋል፡፡ ቡድኑ ሰርጎ በገባባቸው ቦታዎች ‹‹የመከላከያ ሠራዊት የሚገኝበትን ሥፍራ ጠቁሙ›› በሚል ንጹሃንን እያንገላታ እና እየገደለ መሆኑንንም ተናግረዋል፡፡ ሕወሃት ከትላንት በስትያ በደብረ ታቦር ከተማ በተኮሳቸው ከባድ መሳሪያዎች ንጹሃንን መግደሉንም አረጋግጠዋል፡፡
ሕወሓት ከሰሞኑ ፈጽሟቸዋል ስለሚባሉ ጥቃቶችና የንጹሓን ግድያዎች አስመልክቶ ምላሽ ሲሰጥ አይስተዋልም፡፡