አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ነሐሴ 14፣ 2013 ― የአሜሪካው የተራድኦ ድርጅት አስታዳደሪ ሳማንታ ፓወር ‹‹ሕወሓት ወደ ሌሎች ክልሎች የሚፈጽመው ጥቃት ግጭቶችን እና የኢትዮጵያን ሕዝብ ሥቃይ ያራዝመዋል›› ሲሉ የገለጹት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ባስነበቡት መግለጫ ላይ ነው፡፡
አስተዳዳሪዋ በመግለጫቸው ሕወሓት ጥቃቱን በማቆም ኃይሎቹን ከአማራ እና ከአፋር ክልሎች እንዲያስወጣ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ የአማራ ክልላዊ መንግሥት ከምዕራባዊ ትግራይ፣ የኤርትራ መንግሥት ወታደሮቹን ከኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ እንዲያስወጡ ጭምር ጥሪ አቅርበዋል።
በሌላ በኩል ዘጠኝ ወራት ባስቆጠረው የትግራይ ግጭት ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ሳምንት የርዳታ ሰራተኞች ለተቸገረው ሕዝብ የሚያቀርቡት ምግብ ተሟጦ እንደሚያልቅ የገለጹት አስተዳዳሪዋ፣ ይኸው ርዳታ ከሚመሩት የአሜሪካ ተራድዖ ድርጅት፣ አጋሮቹ እና ሌሎች ሰብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢዎች የተገኘ እንደነበር አመልክተዋል፡፡
በጭነት ተሽከርካሪዎች እና በነሐሴ መጀመሪያ በሳምንት በአማካኝ ሁለት የተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ የበረራ አገልግሎት ርዳታ ቢጓጓዝም ‹‹የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦቱ በአስከፊ ሁኔታ አሁንም በቂ አይደለም›› ያሉት ሳምንታ፣ ለተፈጠረው ችግር የኢትዮጵያን መንግሥት ከሰዋል።
ዋና አስተዳዳሪዋ የኢትዮጵያ መንግሥት ሰብዓዊ ርዳታን፣ የሠራተኞች፣ የተሽከርካሪዎች እና የአየር ጉዞዎችን ‹‹አስተጓጉሏል›› ብለዋል። በአፋር ክልል ሰመራ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች የርዳታ ድርጅቶች ምግብ በተሽከርካሪዎች ላይ ጭነው በመጠባበቅ ላይ ቢሆኑም፣ ባለፈው ወር ወደ ትግራይ መግባት የተፈቀደላቸው ግማሽ ያክሉ ብቻ እንደሆኑ የአሜሪካ ተራድዖ ድርጅት መግለጫ ይጠቁማል።
በድርጅቱ መረጃ መሠረት የተቸገረውን ሕዝብ ለመርዳት ምግብ እና ሌሎች ሕይወት አድን አቅርቦቶች የጫኑ 100 ተሽከርካሪዎች በየቀኑ ወደ ትግራይ መድረስ ይኖርባቸዋል። ከሰኔ 24፣ 2013 ወዲህ ባሉት ጊዜያት 5 ሺሕ ተሽከርካሪዎች ትግራይ መድረስ ቢኖርባቸውም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ 320 ብቻ መድረሳቸውን ጠቅሰው ሳማንታ ፓወር በቂ አለመሆኑን ገልጸዋል።