Monday, November 25, 2024
spot_img

ምርጫ ቦርድ በጳጉሜ መጀመሪያ ሊያካሄድ የነበረውን ምርጫ ወደ መስከረም አጋማሽ ለመግፋት ማቀዱ ተሰማ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ነሐሴ 14፣ 2013 ― የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጪው ጷጉሜ 1 ሊያካሄደው የነበረውን ምርጫ ለማራዘም የሚያስችል አዲስ የጊዜ ሰሌዳ ለፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ማቅረቡ ተሰምቷል፡፡ ቦርዱ አዲሱ የድምጽ መስጫ ቀን መስከረም 18፣ 2014 እንዲሆን ምክረ ሃሳብ አቅርቧል ነው የተባለው፡፡

ምርጫ ቦርድ ትላንት ሐሙስ ነሐሴ 13 ከፓለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር በአዲስ አበባ ባደረገው ስብሰባ ላይ በጳጉሜ ሊያደርገው ቀን የቆረጠለትን ምርጫ ላራዝም ነው ለማለቱ ምክንያት ያደረገው የጸጥታ ችግርን መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘገባ ያመለክታል፡፡

ቦርዱ በዚሁ ሰበብ በጸጥታ ምክንያት ምርጫ ለማካሄድ አስቻይ ሁኔታዎች የሉባቸውም ባላቸው የአማራ፣ የኦሮሚያ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ አካባቢዎች ምርጫውን ላልተወሰነ ጊዜ ለማራዘም መወሰኑ ተሰምቷል፡፡ ምርጫ ሊካሄድባቸው እንደሚቻል በተገለጸባቸው የሐረሪ፣ ሶማሌ፣ ድሬዳዋ እና ደቡብ ክልሎች ግን የድምጽ አሰጣጡን በመስከረም 18 ለማድረግ ቦርዱ ማቀዱ ተገልጧል፡፡

ምርጫ ቦርድ ይህን ባሳወቀበት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደረገው ስብሰባ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ‹‹በሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ›› ምክንያት በምርጫው መራዘም ላይ ስምምነታቸውን ገልጸዋል የተባለ ሲሆን፣ በሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ‹‹ምርጫውን መስከረም 18 ማካሄድ አግባብ አይደለም›› የሚል ሃሳብ ጭምር ስለመነሳቱም ተነግሯል፡፡

ይህን ሀሳብ ያነሱ ወገኖች መስከረም ላይ መንግስት ለመመስረት የሚያስችል የፓርላማ መቀመጫ ያገኘ የፖለቲካ ፓርቲ መኖሩን በመከራከሪያነት በማንሳት፣ ምርጫ ባልተከናወነባቸው አካባቢዎች የሚደረገው ምርጫ ‹‹ሀገር በምትረጋጋበት ወቅት መካሄድ አለበት›› ማለታቸውም ተመላክቷል፡፡

የጷጉሜ 1 ምርጫን መራዘምን እንዲሁም ስብሰባ ላይ የተነሱ ጉዳዮችን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኩል ይፋዊ ምላሽ አለመሰጠቱን ዘገባው አመለክቷል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img