Saturday, September 21, 2024
spot_img

ኢትዮ ቴሌኮም በድምጽ እና ጥቅል አገልግሎቶቹ ላይ የታሪፍ ቅናሽ አደረገ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ነሐሴ 13፣ 2013 ― ኢትዮ ቴሌኮም ከነገ ጀምሮ በአጠቃላይ ጥቅል አገልግሎት ላይ የ20 በመቶ ቅናሽ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ ጥቅል ሳይገዙ የድምጽ አገልግሎት ለሚጠቀሙ ደንበኞችም ከ20 እስከ 30 በመቶ የታሪፍ ቅናሽ ማድረጉን ገልጿል።

በኢትዮጵያ ብቸኛው የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ የሆነው ኢትዮ ቴሌኮም ማሻሻያዎች ማድረጉን የገለጸው የ2014 የበጀት ዓመት ዕቅዱን አስመልክቶ ዛሬ ሐሙስ በአዲስ አበባው ሃያት ሪጀንሲ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

ኢትዮ ቴሌኮም ከጥቅል አገልግሎት ጋር የተያያዙ የተለያዩ ማሻሻያዎች ማድረጉን የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በመግለጫው ላይ አስታውቀዋል።

ተቋሙ ከነገ አርብ ነሐሴ 14፤ 2013 ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል ካለው የ20 በመቶ የጥቅል አገልግሎት ቅናሽ ባሻገር፤ ደንበኞች የገዙትን ጥቅል ማጋራት የሚችሉበትን አሰራር እንደሚጀምር ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል። ደንበኞች የገዙትን ጥቅል አገልግሎት፤ ከድምጽ ወደ ኢንተርኔት ወይም ከመልዕክት ወደ ድምጽ፣ ወደ ፈለጉት ጥቅል መቀየር የሚችሉበት አማራጭንም ተቋሙ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጀምርም ጠቁመዋል።

እነዚህ አገልግሎቶች ተግባራዊ መሆን የሚጀምሩበትን ቀን ተቋሙ ወደ ፊት እንደሚያሳውቅም ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል። ደንበኞች የራሳቸውን ጥቅል መቅረጽ የሚችሉበት አሰራርን ግን ከነሐሴ 26 ጀምሮ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጀምር አብራርተዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም 175 የጥቅል አገልግሎት አይነቶች የነበሩት ሲሆን፣ ከእነርሱ ውስጥ “ደንበኞች በብዛት አይጠቀሙባቸውም” የተባሉ የጥቅል አገልግሎቶች እንዲቋረጡ መደረጋቸው በዛሬው መግለጫ ላይ ተመልክቷል። ተቋሙ ከጥቅል አገልግሎት ማሻሻያዎች በተጨማሪ ከሶስት ደቂቃ በላይ የድምጽ አገልግሎት ለሚጠቀሙ ደንበኞችም የታሪፍ ቅናሽ ማድረጉንም ዛሬ ይፋ አደርጓል።

ከሶስት እስከ አስር ደቂቃ የድምጽ አገልግሎት ለሚጠቀሙ ደንበኞች ከመደበኛው ታሪፍ የ20 በመቶ ቅናሽ መደረጉን ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ፍሬህይወት ታምሩ በዛሬው መግለጫ ተናግረዋል። ከአስር ደቂቃ በላይ ለሚጠቀሙ ደንበኞች ደግሞ የ30 በመቶ የታሪፍ ቅናሽ መደረጉንም አክለዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም በ2014 የበጀት ዓመት 70 ቢሊዮን ብር ለማግኘት ያቀደ ሲሆን፣ ይህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ካገኘው ካገኘው የ24 በመቶ ጭማሪ ይኖረዋል ተብሎ ተገምቷል። ተቋሙ ባለፈው ዓመት ያገኘውን 166.5 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬን በሰባት በመቶ የማሳደግ እቅድ ይዟል መባሉን የዘገበው ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ድረ ገጽ ነው፡፡

የፎቶ ምንጭ፡ ኢትዮጵያ ኢንሳይደር

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img