Sunday, September 22, 2024
spot_img

ቱርክ በኢትዮጵያ ጦርነት ተፋላሚ ኃይሎች መካከል እርቅ ለማውረድ ፍላጎት እንዳላት ገለጸች

– ኢትዮጵያ እና ቱርክ በወታደራዊ እና በውሃ ጉዳዮች ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን፣ የስምምነቱ ዝርዝር ለሚዲያ ይፋ አልተደረገም

– ኤርዶጋን ጠ/ሚ ዐቢይን ባገኙበት ቀን የተባበሩት ዐረብ ኤሜሬትስ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ የሆኑት ታሕኑን ቢን ዛይድ አል ናሕያንን ተቀብለው አነጋግረዋል

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ነሐሴ 13፣ 2013 ― የቱርክ ፕሬዝዳንት ረጂብ ጣይብ ኤርዶጋን በኢትዮጵያ ጦርነት ተፋላሚ ኃይሎች መካከል እርቅ ለማውረድ አገራቸው ፍላጎት እንዳላት አሳውቀዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት በትላንትናው እለት ወደ ቱርክ ካቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በተነጋገሩበት ወቅት መሆኑን ለአገሪቱ ገዢ ፓርቲ ቅርብ የሆነው ኤኒውስ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እያለፈችበት ያለውን ሒደት ‹‹ስሱ›› ሲሉ የገለጹት ኤርዶጋን፣ በአፍሪካ አላት ያሉትን ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ እና ጠቀሜታ ጠቅሰው ለአገሪቱ ሰላም፣ ጸጥታ እና አንድነት ትኩረት እንደሚሰጡ አመልክተዋል፡፡

ኤርዶጋን ‹‹የቀጠናውን ሰላም እና መረጋጋት ከመጠበቅ አኳያ ለወቅታዊው ችግር በለዘብተኛ አካሄድ መፍትሔ ማበጀት ያስፈልጋል ብለን እናምናለን›› ያሉ ሲሆን፣ ከዘጠኝ ወራት በላይ ያስቆጠረው ውጊያ ከተባባሰ ዳፋው ለአካባቢው አገራት ሊተርፍ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

ኢትዮጵያ እና ሱዳን የሚወዛገቡበትን የአል ፋሽቃ አካባቢ ጉዳይን ያነሱት ኤርዶጋን፣ ሀገራቸው ሁለቱን ጎረቤታሞች ለማደራደር ፍላጎት እንዳላት ጠቁመዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ ‹‹ውዝግቡ በሁለቱ አገሮች መካከል በሚደረግ ውይይት በመልካም ጉርብትና ላይ በመመስረት እንዲፈታ የልብ ፍላጎቴ መሆኑን ገልጫለሁ። ቱርክ ጉዳዩ በሰላም እልባት እንዲያገኝ ሽምግልናን ጨምሮ ማናቸውንም አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ ናት›› ብለዋል።

የቱርኩ ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ከመገናኘታቸው አንድ ሳምንት ቀድሞ፣ ወደ አንካራ ከተጓዙት የሱዳኑ ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ዐብዱልፈታህ አል ቡርሃን ጋር ተመሳሳይ ውይይት አድርገው ነበር። ከሁለቱ መሪዎች ውይይት በኋላ ኤርዶጋን በሰጡት መግለጫ፤ በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል የተቀሰቀሰው ውዝግብ ‹‹በጋራ ውይይት እና መግባባት›› ሊፈታ ይገባል ብለው ነበር። ሀገራቸው በመጪዎቹ ጊዜያት ከካርቱም ጎን እንደምትቆም ማስታወቃቸውም ይታወሳል።

በትላንቱ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጉብኝት ኢትዮጵያ እና ቱርክ በወታደራዊና በውሃ ጉዳዮች ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን፣ የስምምነቱ ዝርዝር ለሚዲያ ይፋ አልተደረገም።

በቱርክ የነበራቸውን ቆይታ በሰዓታት ውስጥ ያጠቃለሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአንካራ ጉብኝታቸውን አጠናቀው ሲመለሱ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ‹‹የቱርክ መንግስት እና ሕዝብ ያደረገልንን የወሳኝ ጊዜ ትብብር ሀገራችን ኢትዮጵያ መቼም አትረሳውም›› ሲሉ አስፍረዋል፡፡

በሌላ በኩል ኤርዶጋን ሀገራቸው ሽብርተኛ ብላ ከፈረጀችው የሃይማኖት መምህሩ ፌቱላህ ጉለን በምታደርገው ውጊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ኢትዮጵያ ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል። አያይዘውም በፌቱላህ ጉለን ንቅናቄ በኢትዮጵያ ተከፍተው የነበሩ የቱርክ ግንድ ባላቸው ጀርመናውያን ባለሃብቶች ሲተዳደሩ የነበሩ አራት ትምህርት ቤቶች ለቱርኩ ማሪፍ ፋውንዴሽን መተላለፋቸውንም ፕሬዝዳንት አረጋግጠዋል።

በተያያዘ መረጃ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረጀብ ጠይብ ኤርዶጋን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ተቀብለው ባነጋገሩበት በትላንትናው እለት በተመሳሳይ የተባበሩት ዐረብ ኤሜሬትስ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ የሆኑት ታሕኑን ቢን ዛይድ አል ናሕያንን ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

ኤሜሬትስ በቱርክ ስለሚኖራት ኢንቨስትመንት ተደርጓል የተባለውን ንግግር አስመልክቶ በትዊተር ላይ የጻፉት የአገሪቱ ፕሬዝዳንት አማካሪ እና የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንዋር ጋርጋሽ ‹‹ታሪካዊ›› ብለውታል፡፡

በውይይቱ ላይ ኢትዮጵያን የተመለከተ ጉዳይ ስለመነሳቱ ግን የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img