Sunday, October 6, 2024
spot_img

ሂዩማን ራይትስ ዋች በአዲስ አበባ የትግራይ ተወላጆች ላይ እየደረሰ ነው ያለው እንግልት እንዲቆም ጠየቀ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ነሐሴ 12፣ 2013 ― ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ሒዩማን ራይትሰ ዋች በአዲስ አበባ ከተማ የትግራይ ተወላጆች ላይ እየደረሰ ነው ያለው እንግልት እንዲቆም ጠይቋል፡፡

ተቋሙ የሕወሃት ኃይሎች ዳግም ወደ መቀለ ከተማ መመለሳቸውን ተከትሎ ወድያው ጦርነቱን ወደ አጎራባች አማራ እና አፋር ክልሎች በመግፋታቸው በከተማው በትግራይ ተወላጆች ላይ ደርሷል ያለውን የጅምላ እስር እና እንግልት በተመለከተ ሪፖርት አውጥቷል፡፡

ሂዩማን ራይትስ ዋች ለሪፖርቱ ግብአት በሐምሌ እና በተያዘው ነሐሴ ወር ቀድሞ በእስር ላይ የነበሩና አሁን በእስር ቤት ውስጥ ናቸው ያላቸውን ስምንት ታሳሪዎችን በስልክ ማናገሩን ያመለከተ ሲሆን፣ አራት በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ እንዲሁም 25 የታሳሪ ዘመዶችን እና የዓይን እማኞችን አናግሬያለሁ ብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የታሳሪዎችን የፍርድ ቤት እና የክስ ሰነዶችን መመርመሩንም አሳውቋል፡፡

ተቋሙ ባወጣው ሪፖርት የፀጥታ አካላት በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ የትግራይ ተወላጆችን በመንገድ ላይ በማስቆም፣ በካፌዎች፣ በቤታቸው፣ በሥራ ቦታ እና ሌሎች ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ላይ አስቁመው መያዛቸውን አመልክቷል፡፡

የዚህ ሰለባ ሆነዋል ካላቸው መካከል ስማቸውን ያልጠቀሳቸው የትግራይ ተወላጅ የሆኑ የፖለቲካ አንቂ እና የረድኤት ሠራተኛን የጠቀሰ ሲሆን፣ የሚዲያ ባለሞያዎችም ከሰለባዎች መካከል ይገኙበታል ብሏል፡፡

የሂዩማን ራይትስ ዋች የምሥራቅ አፍሪካ ዳሬክተር ላቲሽያ ባደርም የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በቅርብ ሳምንታት በትግራይ ተወላጆች ላይ የጅምላ እስር እና እንግልት መፈጸማቸውን ገልጸዋል፡፡

በነዋሪዎች ላይ ማንነትን በመለየት ለጥርጣሬ እና መድልዎ የሚያጋልጥ ተግባር ተፈጽሟል ያሉት ዳይሬክተሯ፣ ይኸው ተግባር በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡

ሒዩማን ራይትስ ዋች አገኘሁት ባለው ሪፖርት ላይ አስተያየታቸውን ለማወቅ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጌዲዮን ጢሞትዮስ ጋር ኢሜል ባደርግም ምላሽ አልተሰጠኝም ነው ያለው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img