Thursday, November 21, 2024
spot_img

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር የሚሠሩ ሠራተኞች የአንድ ወር ደሞዝ በግዴታ እየተቆረጠ መሆኑ ተሰማ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ነሐሴ 11፣ 2013 ― በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር ባሉ መሥሪያ ቤቶች የሚሠሩ የመንግሥት ሠራተኞች ለመከላከያ ሠራዊት የከተማ አስተዳደሩ ለሚሰበስበው ድጋፍ በግዴታ የአንድ ወር ደሞዛቸውን እንዲሰጡ እየተገደዱ መሆኑን አዲስ ማለዳ ጋዜጣ ነግረውኛል ሲል ዘግቧል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ ስር በሚገኙ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ ደሞዝ እየተከፈላቸው የሚሠሩ የመንግሥት ሠራተኞች የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለመከላከያ ሠራዊት በፈቃደኝነት እንዲሰጡ የሚያዝ ድብዳቤ ቢደርሳቸውም፣ ደብዳቤውና አተገባበሩ ተቃራኒ መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡

ከተማ አስተዳደሩ በስሩ ለሚገኙ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ያስተላለፈውን የድጋፍ ማሰባሠቢያ ቅጽ ‹‹በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ሠራተኞች ለአገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ ማድረጊያ የቃልኪዳን ሰነድ›› በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ነው።

ከተማ አስተዳደሩ ያሰራጨው የቃል ኪዳን ሰነድ ቅጽ፣ የድጋፍ አድራጊውን ሙሉ መረጃ እና በወር የሚያገኘውን የተጣራ ደሞዝ ያካተተ ሲሆን፣ ድጋፉ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ይገልጻል።

ለሠራተኞች የደረሳቸው የድጋፍ ማድረጊያ ቅጽ ‹‹ድጋፍ የሚደረግበት ጊዜ የአንድ ወር የተጣራ ደሞዝ በአንድ ዓመት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ (ከሐምሌ 1/2013 እስከ ሰኔ 30/2014 ድረስ) ይሆና››” ይላል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ ስር ለሚገኙ መሥሪያ ቤቶች የተሰራጨው የድጋፍ ማሰባሠቢያ ቅጹ ሠራተኛው ‹‹ለኢትዮጵያ አገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ የሚሆን በወር ከማገኘው የተጣራ ደሞዜ ላይ በየወሩ እየተቆረጠ በአንድ ዓመት ለመክፈል በፈቃደኝነት የፈረምኩ መሆኑን አረጋግጣለሁ›› ይላል።

ይሁን እንጂ፣ በከተማ አስተዳደሩ ስር በሚተዳደሩ መሥሪያ ቤቶች የሚሠሩ የመንግሥት ሠራተኞች ደሞዛቸው እንዲቆረጥ የፈረሙበት ደብዳቤ ላይ እንደተገለጸው በፈቃደኝነት ሳይሆን ተገደው መሆኑን መጠቆማቸውን ዘገባው አመላክቷል።

ሠራተኞቹ ደብዳቤው ላይ የተገለጸው ግዴታ ከመሆኑ በላይ፣ በፈቃደኝነት ቢሆንም እያንዳንዱ ሠራተኛ በአቀሙ ልክ የፈቀደውን እንዲሰጥ መደረግ እንደነበረበት ተናግረዋል። ከከተማ አስተዳደሩ በተሰራጨው የድጋፍ ማሰባሰቢያ ደብዳቤ የአንድ ወር የተጣራ ደሞዝ ስለሚል፣ የአንድ ወር ደሞዛቸውን ድጋፍ ለማድረግ አቅም የሌላቸውና ፈቃደኛ ያልሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች በተቀበሉት ደብዳቤ ላይ እንደየአቅማቸው ከአንድ ወር ደሞዛቸው በታች ሞልተው ቢልኩም፣ አይቻልም ተብሎ እንደተመለሰባቸው ገልጸዋል።

የደሞዛቸውን 20 እና 50 በመቶ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆናቸውን በፊርማቸው ያረጋገጡ የመንግሥት ሠራተኞች አይቻልም ተብለው ሙሉ የአንድ ወር የተጣራ ደሞዛቸወን ለመስጠት እንዲፈርሙ ዳግመኛ ደብዳቤ እንደደረሳቸው ነው የተነገረው፡፡ ይህን ለማድረግ ፍቃደኛ ያልሆኑ የመንግሥት ሠራተኞች ጊዜ ድረስ የሐምሌ ወር ደሞዛቸው እንዳልተለቀቀላቸው ተናግረዋል። ደሞዛቸው ካልተለቀቀላቸው የመንግሥት ሠራተኞች ውስጥ መምህራን ይገኙበታል ነው የተባለው፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ ‹‹መንግሥት ቀድሞ ከካዝናው 734 ሚሊዮን ብር ከፍሏል››› ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕሬስ ሴክሬተሪ ባለሙያ የሆኑት ስንታየሁ ደርቤ ተናግረዋል። አጠቃላይ የመንግሥት ሠራተኞች ደምወዝ እንዲቆረጥ ሁሉም ቀድሞ ተስማምቷል የሚሉት ስንታየሁ፣ ቅሬታ መቅረብ የነበረበት ቀድሞ ነበር፣ አሁን ላይ መንግሥት ከካዝናው ስለከፈለ ደሞዝ መቆረጡ ግዴታ ነው ማለታቸውንም ዘገባው አክሏል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img