አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ነሐሴ 8፣ 2013 ― የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ከዐርብ ነሐሴ 7፣ 2013 ጀምሮ ለመሬት አስተዳደር ተቋማት፣ ለመሠረተ ልማት ቅንጅት እና ግንባታ ፈቃድ ባለስልጣን እንዲሁም ለ11ዱም ክፍለ ከተሞች ባስተላለፈው ሰርኩላር፣ የመሬት እና የመሬት ነክ አገልግሎቶች ላልተወሰነ ጊዜ ሙሉ በሙሉ እንዳይሰጡ ውሳኔ ማስተላለፉን አሳውቋል።
ካቢኔው ዕግዱን ያስተላለፈው በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ትኩረታቸውን በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በማድረግ መሆኑን የገለፀ ሲሆን፣ አንዳንድ ስግብግብ ያላቸው ግለሰቦች ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታውን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም በአቋራጭ ለመክበር በመሬትና መሬት ነክ አገልግሎቶች ላይ ትኩረት በማድረግ በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውን የከተማ አስተዳደሩ መገንዘቡንም አመልክቷል።
በዚህም ምክንያት ማንኛውም መሬትና መሬት ነክ አገልግሎት ላልተወሰነ ጊዜ መታገዱን ነው የገለጸው።