Tuesday, October 15, 2024
spot_img

ሕወሓት እና ኦነግ ሸኔ የመጣመራቸው ዜና የሚያስገርም አለመሆኑን አቶ ታዬ ደንደኣ ተናገሩ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ነሐሴ 5፣ 2013 ― በኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጁት ሕወሓት እና ኦነግ ሸኔ የመጣመራቸው ዜና የሚገርም አለመሆኑን የብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ጽሕፈት ቤት ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ታዬ ደንደኣ ተናግረዋል፡፡

ከአሜሪካ ድምጽ ጋር ባደረጉት ቆይታ ሁለቱ ቡድኖች ‹‹አንድም ጊዜ ተለያይተው አያውቅም›› ያሉት አቶ ታዬ፣ ‹‹ሸኔ ኦሮሚኛ ቋንቋ የሚናገር ወያኔ›› እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

የሕዝብ ግንኙነቱ እርሳቸው ራሳቸውም ከዚህ ቀደም በሐረር መስመር 42 ተማሪዎችን ይዘው ኦነግ ሸኔ የሚባለውን ቡድን ለመቀላቀል ተንቀሳቅሰው እንደነበር የተናገሩ ሲሆን፣ ይህንኑ እውነታ በወቅቱ እንደተረዱ አመልክተዋል፡፡

ላለፉት ጊዜያት ኢትዮጵያውያንን ሲያጠቁ ነበሩ ያሏቸው ሁለቱ ቡድኖች የመዋሃዳቸው ዜና በተለይ ‹‹ሸኔ ይታገልልናል የሚሉትን ያነቃል ብዬ አስባለሁ›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

ሁለቱ ቡድኖች ቀድሞ አብረው ሲሠሩ ይሠሩበት ነበር ባሉት ወቅትም ‹‹ኦሮሞን ለማሰቃየት›› ሕወሓት ‹‹የኦነግ ታርጋ›› ይለጥፍ ነበር ያሉ ሲሆን፣ በሕወሓት አገዛዝ ዘመን አንድም ጥይት አልተኮሰም ያሉት ሸኔ የሚባለው ቡድን፣ ውጊያ የጀመረው ‹‹ወያኔ ሲወርድ›› መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

በመንግሥት ኦነግ ሸኔ የሚባለውና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ሲል የሚጠራው ቡድን መሪ ነው የሚባለው ኩምሳ ድሪባ ወይም ጃል መሮ ነግሮኛል ብሎ አሶሽየትድ ፕረስ እንደዘገበው፣ ለፌዴራል መንግስቱ ‹‹አሁን ያለው ብቸኛ መፍትሔ እንዲነገራቸው በሚፈልጉት ቋንቋ በማናገር የመንግስትን ሃይል መጣል ነው›› ብሏል፡፡ ለዚህም ‹‹በአንድ ዐይነት ጠላት ላይ ለማበር›› ከሕወሓት ጋር መስማማታቸውን ገልጧል፡፡

በፌዴራል መንግስት በሽብረተኝነት የተፈረጀው ሕወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በተመሳሳይ ለሬውተርስ የዜና ወኪል ‹‹ከቡድኑ ጋር የሆነ ዐይነት ስምምነት ላይ ለመድረስ እየሰራን ነው›› በማለት ዝርዝሩን ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለሚከሰቱ የንጹሐን ጥቃት አሁን መጣመራቸው የተነገረውን ራሱ እንደሚጠራው ኦነግ ሸኔ እና ሕወሓትን ሲወነጅል መሰንበቱ ይታወቃል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img