አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ነሐሴ 6፣ 2013 ― የሕወሓት ኃይሎች የፌዴራል መንግሥት እንዲፈጽመው እንፈልጋለን ያሏቸው ቅድመ ሁኔታዎችና በሕዝብ ላይ ተጥሏል ያሉት ‹‹ከበባ›› እስኪነሳ ድረስ ውጊያውን እንደሚቀጥሉ ቃል አቀባዩ አቶ ጌታቸው ረዳ ገልጸዋል፡፡
አቶ ጌታቸው ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ግጭቱን የት ድረስ ነው የምትወስዱት፤ እስከ አዲስ አበባ የመሄድ ሃሳብ አላችሁ ወይ ተብሎ ለተነሳላቸው ጥያቄ፣ ‹‹ያስቀመጥናቸው ቅድመ ሁኔታዎችና በሕዝባችን ላይ የተጣለው ከበባ እስኪነሳ ድረስ፤ ያልተገደበና ያልተቆራረጠ የሰብዓዊ ዕርዳታ ተደራሽነት፣ ሙሉ በሙሉ የራሳችንን ዕጣፈንታ በራሳችን መወሰንና የመሳሰሉት እስኪሟሉ ድረስ እንቀጥላለን›› ሲሉ መልሰዋል፡፡
በሌላ በኩል በዚሁ ቆይታቸው የሰብአዊ ሁኔታን ያነሱት አቶ ጌታቸው ‹‹በመቀለ አቅራቢያ የሆኑ አካባቢዎች ላይ ሰዎች በምግብ እጥረት ምክንያት እየሞቱ መሆናቸውን እየሰማን ነው›› ብለዋል፡፡
‹‹መናገር የምፈልገው ስልክ የለም፣ መብራት ተቋርጧል፣ ባንክ ተቋርጧል›› ያሉት ጌታቸው፣ ‹‹ይህ ማለት በየቀኑ ኑሯቸውን ለማሸነፍ በተለያየ ሥራ ተሰማርተው የነበሩ ነዋሪዎች ተቸግረዋል፤ ገንዘባቸውን ከባንክ እንዳያወጡ ተደርገዋል፤ በችግርና በስቃይ ላይ ስላለው ሕዝባችን መረጃ ለማግኘት የተገደበና የተወሰነ ነው፤ በጣት የሚቆጠሩ የሳተላይት ስልኮች ብቻ ናቸው ያሉን›› ማለታቸውም ተመላክቷል፡፡
ከተጀመረ ስምንት ወራት ያለፉት በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰው ጦርነት በቅርብ ቀናት ወደ አጎራባች አፋር እና አማራ ክልሎች መስፋፋቱ መነገሩ ይታወሳል፡፡ አቶ ጌታቸው ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ‹‹በቁጥጥራችን ስር ናት›› ካሏት ወልዲያ እና አቅራቢያ ያሉ ሰዎች ተፈናቅለው ወደ ደሴ መክተማቸው እየተነገረ ይገኛል፡፡
የአማራ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በበኩላቸው በሕወሓት ኃይሎች ተይዘው የነበሩ በሰሜን ወሎ የሚገኙ ከተሞች በውጊያ ነፃ መውጣታቸውን ለሚዲያዎች ተናግረዋል፡፡ በወልዲያ ውጊያ መኖሩን የገለጹት አቶ ግዛቸው፣ ‹‹ድል እየተገኘ ነው›› ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል ጨጨሆን ተሻግሮ መቄት አካባቢ ከባድ ውጊያ ተደርጓል ያሉ ሲሆን፣ ‹‹በዚህም የሕወሓት ኃይሎ›› ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶባቸዋል ነው ያሉት፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በበኩሉ ከትላንት በስትያ ነሐሴ 4 ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ተነስቷል ያለውን የሕወሓት ኃይል እና የውጭ እጆች ስውር ደባ ለመደምሰስ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የክልል ልዩ ኃይሎችና ሚሊሻዎች ብርቱና ‹‹የማያዳግም ክንዳችሁን እንድታሳርፉ›› የሚል አቅጣጫ መቀመጡን አስታውቋል፡፡