Monday, October 14, 2024
spot_img

በትግራይ ክልል ኤርትራዊያንን ያስጠለሉ ጣቢያዎች ለርዳታ ሠራተኞች በድጋሚ ተደራሽ ሆነዋል ተባለ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ነሐሴ 5፣ 2013 ― በትግራይ ክልል የሚገኙት ማይ አይኒ እና አዲ ሐሩሽ የተባሉት የኤርትራውያን ስደተኛ መጠለያዎች ለርዳታ ሠራተኞች እንደገና ተደራሽ መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) አስታውቋል፡፡

ድርጅቱ ካለፈው ሳምንት ሐሙስ ጀምሮ በሁለቱ የስደተኛ መጠለያዎች ለተጠለሉ 23 ሺህ ያህል ስደተኞች የሚያስፈልገውን አስቸኳይ ርዳታ ማቅረብ ጀምሬያለሁ ብሏል።

የዩኤንኤችሲአር ቃል አቃባይ ቦሪስ ቼሺርኮቭ ዛሬ በስዊዘርላንድ ጄነቫ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳሉት፤ ሁለቱ የስደተኛ መጠለያዎች ባሉበት አካባቢ የነበረ ግጭት የድርጅቱን ሰራተኞች ከሐምሌ 6 ጀምሮ ወደ መጠለያ ጣቢያዎቹ እንዳይደርሱ አግዷቸው ቆይቷል።

በዚህም ምክንያት ኤርትራውያን ስደተኞች አስከፊ ሁኔታዎችን መጋፈጥ መቀጠላቸውን ቃል አቃባዩ ጠቁመዋል።

ዩኤንኤችሲአር እና አጋሮቹ፤ በትግራይ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች የነፍስ አድን ሰብዓዊ እርዳታ እና ጥበቃ ያቀርቡ ዘንድ፤ በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት በክልሉ ያልተገደበ ተደራሽነትን ማረጋገጥ እንዳለባቸውም ቃል አቃባዩ አሳስበዋል።

በሌላ በኩል ድርጅቱ በሁለቱ መጠለያ ጣቢያዎች ያሉ ስደተኞችን አዲስ ወደተዘጋጀላቸው ስፍራ ለማዘዋወርም ደህንነቱ የተጠበቀ መንገድ እንዲመቻችለት ጥሪ አቅርቧል። አዲስ የተዘጋጀው የአለምዋጭ የስደተኞች መጠለያ በአማራ ክልል ዳባት ከተማ አቅራቢያ የሚገኝ ነው።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img