Sunday, September 22, 2024
spot_img

ከሰሜን ወሎ ተፈናቅለው ወደ ደሴ እየገቡ ያሉ ተፈናቃዮች ቁጥር እያሻቀበ እንደሚገኝ ተነገረ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ነሐሴ 4፣ 2013 ― ከሰሜን ወሎ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ግጭቱን በመሸሽ በርካታ ተፈናቃዮች ወደ ደሴ እየገቡ እንደሚገኙ እና በከተማዋ መጨናነቅ እንደተፈጠረ የደሴ ከተማ ከንቲባ አቶ አበበ ገ/መስቀል ገልጸዋል፡፡

አቶ አበበ በደሴ ከተማ ተጠልለው ከሚገኙት ተፈናቃዮች መካከል ማረፍያ ያላቸው በየዘመድ ቤት መጠጋታቸዉን ጠቅሰው አብዛኛው ሰው ግን የደሴ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ባዋቀረው እና በምክትል ከንቲባው በሚመራው ኮሚቴ አማካኝነት በትምህርት ቤቶችና ሌሎች ተቋማት ውስጥ ወደተዘጋጁ ስድስት መጠለያዎች ቦታዎች ገብተው የመጠለያና የአልባሳት ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ነግረውኛል ብሎ አዲስ ዘይቤ ዘግቧል፡፡

ተፈናቃዮቹ ከቆቦ፤ ከወልዲያና ከመርሳ አካባቢዎች ወደ ደሴ መግባታቸዉን የሚገልጹት ከንቲባዉ አስከ ትላንትናዋ ቀን ድረስ በደሴ ከተማ ከ24,000 በላይ ተፈናቃች መመዝገባቸውን አመልክተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ዛሬን ጨምሮ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው ወደ ከተማዋ በመግባት ላይ ስለሚገኝ ይህ ቁጥር ሊያሻቅብ ይችላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ወደ አጎራባቿ የኮምቦልቻ ከተማም ቁጥሩ ቀላል የማይባል ሰው እየገባ አንደሚገኝም ታውቋል፡፡

በደሴ ከተማ አካባቢ ያለውን የጸጥታ ሁኔታ በተመለከተ የተጠየቁት ከንቲባው፣ ‹‹የተፈናቃዮቹ ቁጥር ከፍተኛ መጨናነቅን ከማስከተሉ ውጪ የደሴ ከተማ የፀጥታ ሁኔታ ሰላም ላይ ነው የሚገኘው፤ በከተማዋ እስካሁን ያጋጠመ የጸጥታ ችግር የለም›› ማለታቸውም ተመላክቷል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img