አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ሐምሌ 8፣ 2013 ― የኢትዮጵያ ኮምዩኒኬሽን ባለሥልጣን ለአዲሱ የቴሌኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ባለፍቃድ ያስቀመጠውን መስፈርት መሰረት በማድረግ ፍቃድ መስጠቱን አሳውቋል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ባልቻ ሬባ ‹‹ሳፋሪኮም ቴሌኮምዩኒኬሽንስ ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር›› በጊዜ ገደብ የተጠናቀቀውን ጊዜያዊ የፈቃድ ስምምነት በስሙ አዙሯል ብለዋል፡፡
በዚህም መሰረት ሳፋሪኮም ቴሌኮምዩኒኬሽንስ ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከሐምሌ 2፣ 2013 ጀምሮ ለ15 ዓመት ጸንቶ የሚቆይ እና እንደ ሁኔታው ታይቶ በ15 ዓመቱ የሚታደስ የአገልግሎት ፈቃድ ተሰጥቶታል፡፡
ኩባንያው በሃገር አቀፍ ደረጃ ሙሉ አገልግሎት ለማቅረብ የተቀናጀ የቴሌኮምዩኒኬሽን ፍቃድ ማግኘቱ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ኮምዩኒኬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ባልቻ ሬባ እንደገለፁት የኢትዮ-ቴሌኮምን ከፊል ድርሻ ለግሉ ዘርፍ ለመሸጥ የሚደረገው እንቅስቃሴ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡