Monday, November 25, 2024
spot_img

ለኤድና ሞል ግዢ 810 ሚሊዮን ብር ቀረበ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ሐምሌ 7፣ 2013 ― በቅርቡ ባለቤቱ ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንድ የተበደረውን ገንዘብ ባለመክፈሉ ለሐራጅ ሽያጭ የቀረበው ኤድና ሞል ለግዢው 810 ሚሊዮን ብር ቀርቦለታል፡፡

ፎርቹን ይዞት እንደወጣው መረጃ ከሆነ ለኤድና ሞል ይህን ያህል መጠን ያቀረበው በቻይናውያን ባለቤትነት የሚተዳደረው ኢስት ስቲል ነው፡፡

በ2 ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈውንና በተለይ የፊልም ተመልካቾች የሚያዘወትሩትን ሕንጻ ለመግዛት አምስት ተጫራቾች መቅረባቸው ሲነገር፣ ከጨረታው ተፎካካሪዎች መካከል ሁለቱ ሙሉጌታ መኮንን እና ደሳለኝ ፈንቴ የተባሉ የግል ባለሐብቶች ናቸው፡፡

አቶ ሙሉጌታ ኢስት ስቲል ካቀረበው በአስር ሚሊዮን ብር ብቻ ያነሰ ገንዘብ ማቅረባቸው ሲሰማ፣ ደሳለኝ ፈንቴ በበኩላቸው 750 ሚሊዮን ብር አቅርበዋል፡፡

የጨረታው ሌላኛው ተፎካካሪ ሆኖ የቀረበው ኮሜርሻል ኖሚኒስ 700 ሚሊዮን ብር ያቀረበ ሲሆን፣ ቀድሞ በጨረታው ለመሳተፍ እቅድ የነበረው ኅብረት ባንክ ደግሞ ለጨረታው የቀረበው ገንዘብ ካቀድኩት በላይ ነው በሚል ምንም ገንዘብ ሳያቀርብ ቀርቷል፡፡

የወከላቸው ባንክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ከፍቶበት የሕንጻውን ቀሪ ክፍሎች ለማከራየት አቅዶ እንደነበር የገለጹት የኅብረት ባንክ ተወካይ አቶ ቱሉ ዴሬሳ፣ 237 ሚሊዮን ብር መነሻ ለተያዘለት ሕንጻ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ይቀርባል ብለው እንዳልጠበቁ ተናግረዋል፡፡

ጋዜጣው ኅብረት ባንክ ባለፈው ዓመት ያተረፈው አንደኛው የሕንጻው ተጫራች ኢስት ስቲል ካቀረበው 810 ሚሊዮን፣ በ84 ሚሊዮን ብር ብቻ ብልጫ ያለው 894 ሚሊዮን ብር ማትረፉን አስታውሷል፡፡

የኤድና ሞል አስተዳደር ሆነው ያገለገሉት ውብሸት አበራ በበኩላቸው ለሕንጻው ከአንድ ቢሊዮን ብር በታች ይቀርባል የሚል ግምት እንዳልነበራቸውና የቀረበው ከገመቱት ያነሰ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የጨረታውን ሒደት አስመልክቶ ከኤድና ሞልም ሆነ ሻጩ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል የተባለ ነገር የለም፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img