Saturday, September 21, 2024
spot_img

ኢትዮ ቴሌኮም በትግራይ ክልል የቴሌኮም አገልግሎት ለማስቀጠል ከሚመለከታቸው ጋር እየመከርኩ እገኛለሁ አለ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ሐምሌ 7፣ 2013 ― በትግራይ ክልል የቴሌኮም አገልግሎት ለማስቀጠል ከመንግሥትና ባለድርሻ አካላት ጋር በመነገጋገር ላይ እንደሚገኙ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ ገልጸዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በተለይም በትግራይ ክልል ከፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ በቴሌኮም መሰረት ልማት ላይ ጉዳት መድረሱን አስታውሰዋል።

በሰሜን ሪጅን የቴሌኮም አገልግሎትን ለማቅረብ በክልሉ ያሉ 652 ቢቲኤስ ማሰራጫዎችን ለመጠገን፣ ኃይል አቅርቦት እንዲያገኙ ለማድረግ እና ጄኔሬተሮችን ነዳጅ መሙላት ያስፈልጋል ብለዋል።

እንዲሁም ደንበኞች የአየር ሰዓት መግዛት እንዲችሉ የአየር ሰዓት የሚያከፋፍሉ የኢትዮ ቴሌኮም ወኪሎች ጋር የአየር ሰዓት መላክ እና ገንዘብ ልውውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል ችግሩ ከተከሰተ በኋላ ኢትዮ ቴሌኮም በተወሰነ ደረጃ ጥገናዎችን በማከናወን አገልግሎት ሲሰጥ እንደነበረም አስታውሰዋል።

ሆኖም በቅርቡ በድጋሚ በተፈጠረው ችግር በኋላ ኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎቱን ለማስጀመር ስራውን ከበርካታ ባለድርሻ አካላት ጋር ስለሚሰራ የቴሌኮም አገልግሎትን ለማስቀጠል አስቸጋሪ እንደሆነበት አንስተዋል።

አሁን ላይ ተቋሙ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት እና ባለድርሻ አካላት ጋር የቴሌኮም አገልግሎቱን እንዴት ማስቀጠል ይቻላል የሚለው ላይ እየተነጋገረ መሆኑን ገልጸዋል። በክልሉ ያሉ የተቋሙ ሰራተኞች ለጥገና፣ አገልግሎት ለመስጠት እና መንቀሳቀስ የሚችሉበት ሁኔታን ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑም ተገልጧል፡፡

በትግራይ ክልል የአገር መከላከያ ሠራዊት መቐለ ከተማን መልቀቁን ተከትሎ የቴሌኮምን ጨምሮ ሌሎች መሠረታዊ የሚባሉ አገልግሎቶች መቋረጣቸው መነገሩ ይታወቃል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img