አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ሐምሌ 6፣ 2013 ― የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመብቶች ጉባኤ በትግራይ ክልል ግጭት ያባብሳሉ ያላቸው የኤርትራ ወታደሮች የኢትዮጵያን መሬት ለቀው እንዲወጡ በአውሮፓ ኅብረት ተወካይ የቀረበለትን የውሳኔ ሐሳብ አሳልፏል፡፡
ይኸው የውሳኔ ሐሳብ በጉባኤው በሚገኙ 20 አባላት ድጋፍ ያገኘ ሲሆን፣ 14 ተቃውሞ እና 13 ድምጸ ተዐቅቦ አስተናግዷል፡፡
በጉባኤው ወታደሮቿን እንድታስወጣ የሚል ድምጽ የተሰጠባትና አባል የሆነችው ኤርትራ በተወካይዋ በኩል ውሳኔውን እንደተቃወመች ሲነገር፣ ከ47ቱ አባል አገራት መካከል ያልሆነችው ኢትዮጵያ ምንም እንኳ ድምጽ የመስጠት መብት ባይኖራትም ተወካይዋ ግን ውሳኔውን እንደሚቃወሙት መናገራቸወውን ሬውተርስ ዘግቧል፡፡
የኢትዮጵያ ተወካይ ውሳኔው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከመንግሥታቱ ድርጅት የመብቶች ጉባኤ ጋር በትግራይ የሚያደርገው የሰብአዊ መብቶች ምርመራ ላይ አሉታዊ ውጤት የሚያስከትል መሆኑን ገልጸዋል ነው የተባለው፡፡
በጉባኤው ላይ የውሳኔውን ሐሳብ ከተቃወሙት መካከል የሆኑት የቻይናው ተወካይ፣ የውሳኔ ሐሳቡ ቀድሞውኑ ችግር ያለበት መሆኑን ገልጸው፣ ምናልባትም በትግራይ ያለውን ሁኔታ ሊያባብሰው የሚችል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫም ወቅቱን ያልጠበቀ ነው ያለውን በጉባኤው የተላለፈውን ውሳኔ የተቃወመ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከመንግሥታቱ ድርጅት የመብቶች ጉባኤ ጋር የሚያደርጉትንና በነሐሴ ወር ይፋ ይደረጋል በተባለው የትግራይ ክልል የሰብአዊ መብቶች ምርመራን የሚያሳንስ ነው ብሎታል፡፡