Saturday, September 21, 2024
spot_img

ኢትዮ ቴሌኮም በ2013 በጀት ዓመት 56 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አሳወቀ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ሐምሌ 6፣ 2013 ― ኢትዮ ቴሌኮም በ2013 በጀት ዓመት 56 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ተናግረዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ የሞባይል ስልክ የድምጽ አገልግሎት ደንበኞች ቁጥር ወደ 54 ነጥብ 3 ሚሊዮን ማደጉንም ገልጸዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ይህን የተናገሩት የተቋሙ የ2013 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸም በተመለከተ በአዲስ አበባው ሃያት ሬጀንሲ ሆቴል በሰጡት መግለጫ ላይ ነው። ተቋሙ በበጀት ዓመቱ ለማስገባት አቅዶ የነበረው ገቢ 55 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር እንደነበር የጠቀሱት ፍሬሕይወት፤ ‹‹ከዕቅዳችን በላይ 101 ነጥብ 7 በመቶ ማሳካት ችለናል›› ብለዋል።

ከአጠቃላይ ገቢው ውስጥ 47 ነጥብ 5 በመቶ የተገኘው ከሞባይል የድምጽ አገልግሎት መሆኑን የገለጹት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ፤ ዳታ እና ኢንተርኔት ደግሞ 27 በመቶ ያህሉን የገቢ ድርሻ መያዛቸውን አስረድተዋል። ተቋሙ በየጊዜው ያደረገው የታሪፍ ማሻሻያ ተቋሙ ከዕቅዱ በላይ ገቢ እንዲያስገባ እንዳስቻለውም ጠቁመዋል።

ከድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር ተያይዞ በመላ አገሪቱ የኢንተርኔት መቋረጥ በመከሰቱም ተቋሙ በቢሊዮን የሚቆጠር ገቢ ማጣቱንም ገልጸዋል። ‹‹ክስተቱ የ2013 በጀት ዓመት መጀመሪያ ላይ መከሰቱ ያልጠበቅነው ነበር›› ሲሉም ፍሬሕይወት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ብቸኛው የቴሌኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሰጪ የሆነው ኢትዮ ቴሌኮም፤ ባለፉት ሶስት ዓመታት ብቻ የ48 ነጥብ 2 በመቶ የደንበኞች እድገት መመዝገቡን አስታውቋል።

በሐምሌ 2010 የነበረው የ37 ነጥብ 92 ሚሊዮን የቴሌኮም ተጠቃሚ ቁጥር፤ በሰኔ 2013 ወደ 56 ነጥብ 2 ሚሊዮን ማደጉም በዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ተገልጿል። ኢትዮ ቴሌኮም ከ2010 ጀምሮ ያደረገው ማስፋፊያ የተጠቃሚዎች ቁጥር እንዲጨምር አስተዋጽኦ አድርጓል መባሉንም የዘገበው ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ነው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img